ኢትዮጵያዊውን ስስ ብልቱን በእሳት እያቃጠሉ ሲጫወቱበት ቆይተው ገደሉት፣…ሌላኛው እጁ ከክንዱ ተላቆ ከጥቅም ውጭ ሆነ

የIOM ሰራተኞችም ከአፋኞቹ ጋር ግንኙነት እንደላቸው ኮሎኔል አሊ ኡመር ገለጹ

                                    በግሩም ተ/ሀይማኖት

የየመን መንግስት ሰሞኑን በወሰደው ጥብቅ እርምጃ ባህር ተሻግረው የሚገቡት ኢትዮጵያዊያንን የሚያግቱት ላይ ተደጋጋሚ ጥቃት ሰንዝሯል፡፡ ባለፈው እሁድ እለት በአፋኞቹ ላይ በተደረገ ከበባ 180 ኢትዮጵያዊያን መለቀቃቸውን የድንበሩ አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ገለጹ፡፡ እኝሁ ባለስልጣን ኮረኔል አሊ ኡመር ይስለም ለአል-መስዳር ጋዜጣ ሪፖርተር ሲገልጹ ‹‹ጠንካራ ዘመቻ እና ትግል አድርገናል›› ብለዋል፡፡ ‹‹…2 ብርጌድ የተውጣጣ ወታደር፣ ድንበር የለሽ የህክምና ቡድን፣ የክፍለሀገሩ ደህንነት፣ ድንበር ጠባቂዎች…ሆነን በ11 መኪና ሞልተን ነው ዘመቻውን ያካሄድነው፡፡ ከአንድ ጊቢ ውስጥ ብቻ 180 ኢትዮጵያዊያን በአፋኞች ተይዘው ተገኝተዋል፡፡ አፋኞቹ ውስጥ 3 ያህሉ የአለም አቀፉ ስደተኞች ድርጅት IOM ሰራተኞች ሆነው ተገኝተዋል፡፡…›› ሲሉ አጃኢብ ያሰኘ ወሬ አድርሰውናል፡፡
    ለመሆኑ ኢትዮጵያዊያኑ ላይ ከእግዚአብሄር ውጭ ሁሉ የጨከነባቸው ለምን ይሆን? ከራሳቸው ሀገር መንግስት ጀምሮ ኤምባሲ፣ የመገናኛ ብዙሀኑ፣ ለጩኸቱ ምላሽ የነፈገው ህዝብ…ማህበራዊ ድረ-ገጾቹ ስደተኛው ላይ አደጋ ደረሰ ሲባል ዜና መጻፍ አለመፈለጋቸውን ጭምሮ ማን ይሆን አስታዋሹ?… ምነው እንባችን ስፍር አልሞላ ብሎ ይሆን እያለቀስን እንድንኖር የተወሰነብን? መንግስት አባይን ብቻ ሳይሆን የዜጎቹን እንባም ሊገድብ ይገባል፡፡
    ወደ ዘገባዬ ልመለስና ኮሎኔሉ ‹‹በስደተኞቹ የማረፊያ ካምፕ ውስጥ አስተርጓሚ ሆነው የሚሰሩት እነዚህን ሰዎች ለአፋኞቹም አስተርጓሚ ሆነው የሚያገለግሉ ናቸው፡፡ ስደተኞቹንም ከካምፕ አውጥተው ይሸጡላቸዋል፡፡ በሁኔታቸው ተጠራጥረን ተከታተልናቸው እውነትም ሆኖ አገኘናቸው..›› በማለት ገልጸዋል፡፡
     የአል-መስዳር ጋዜጣ ሪፖርተር ስላየው ሁኔታ ሲገልጽ ደግሞ ታጋቾቹ ኢትዮጵያዊያን ነጻ ከወጡ በኋላ ያለውን እንዲህ አስፍሮታል፡፡ ‹‹…ያረፉበት ጊቢ ስገባ 7 ሴቶች አየሁ፡፡ ድካም እና ርሀብ በጉልህ ይታይባቸዋል፡፡ ያሳዝናሉ የሚለውም ከሚገልጸው በላይ ናቸው፡፡ ከሰባቱ አንደኛዋ አራስ ነበረች፡፡ ከወለደች ስድስት ቀኗ ነው፡፡ (ለ16 ቀናት ያህል በአጋቾቹ እጅ ስለ ቆየች በድብደባ ያለጊዜው እንደ ወለደች ይገምታል፡፡) በሙቀቱና በርሃብ ልጇ እንዳይሞትባት ፈርታለች፡፡ ርሀቡን እሷም መቋቋም አቅቷታል፡፡ የጣቢያው አዛዥ ጠጋ ብሎ ‹‹ተመልከት›› አለኝ፡፡ ለደከሙት የተሻለ ክፍል ፖሊሶቹ ሰጥተዋቸዋል፡፡ የፖሊሱ አዛዥ እንደሚለው ከሆነ ‹‹…ይህን አይነት አሰቃቂ ነገር እኛ በየጊዜው ከማየት የተነሳ የለመድነው ሁሌ የምናየው ነው፡፡
    አፍሪካውያኑ ስደተኞች ወደዱም ጠሉም የእነሱ ግብ የሆነው ሀገር (ሳዑዲ አረቢያ ማለታቸው ነው) ለመሄድ ያለው መንገድ ይሄ ብቻ ነው፡፡ እኛም ወደድንም ጠላንም የተጎዱትን ማየቱን ተገደናል፡፡ ለምደነዋል፡፡ በጣም የሚገርመው እና የሚያሳዝነው ከ100 ኪሎ ሜትር በላይ በማይታመን እና ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ሲጓዙ ማየት የተለመደ ነው፡፡ ይህን ሁሉ ጊዜ ሲጓዙ ከሞት ጋር እየታገሉ ነው፡፡ በፈለጉ ሰዓት ሽፍቶች እየያዙ ይጫወቱባቸዋል፡፡ ይገሏቸዋል፡፡ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩትም እየሞቱ በየመንገዱ ይቀራሉ፡፡ (ሬሳም በየቦታው ይታያል) ከቻሉ አሸዋውን ጫርጫር አድርገው ይቀብሯቻል፡፡ (ይህንን እድል ማግኘት መታደል ነው፡፡ አውሬ ነው የሚበላቸው ወይም አካባቢው ላይ ሽታ ሲያስቸግራቸው ይቀብሯቸዋል)
    በውሀ ጥም፣ በርሃብ ይሞታሉ፡፡ ከሞት የተረፉትም ቢሆን ቋንቋ እንኳን በቅጡ ባለማወቃቸው በምልክት ብቻ ነው የሚበላ የሚጠይቁት፡፡ በርሃብ ተጎድተው ነው የሚደርሱት፡፡ አለ-መሀዝ የምትባለ ቦታ ላይ እንደልብ ሱቅ እና እቃ መግዣ ቦታ የለም፡፡ እዚህ አካባቢ ምግብ ቤት ገብተህ መብላት አትችልም፡፡ ይህን ሁሉ መከራ ሊቀበሉ ግድ ያላቸው ከሚመጡበት ሀገር (ከኢትዮጵያ ማለታቸው ነው) ስቃይ እና ግፍ ችግር ስላለባቸው ነው፡፡…(ስቃይና ችግር መኖሩማ ነው እያሰደደ ቁጭ ብሎ ከመሞት ወይ ይለፍልኝ ወይ ይለፍብኝ ብለው ወደ ሞት የሚነጉዱት አማርኛ ቢችሉና የሎሬየት ፀጋዬ ገ/መድህንን ‹‹ርሃብ ስንት ቀን ይሰጣል›› የሚለውን ቢያነቡ ይህን ባላሉ) ይህን ስቃይ እና ችግራቸውን ለማሳየት ወደ እዛ የሄዱ የመገናኛ ብዙሀን ባለሞያዎች ያናገሯቸውን በሙሉ ለህዝብ ማውጣት አልቻሉም፡፡ በጣም ሰቅጣጭ በመሆኑ ህዝቡን መረበሽ ነው ብለው አለፉት፡፡
     የተጓዡ መጠን በጨመረ ቁጥር የሚገርመው የአፋኞቹም ቁጥር መጨመር ብቻ ሳይሆን መደራጀት እና ማን አለብኝነት ከመሰማቱ በላይ ከ IOM ካምፕ ውስጥ ሁሉ ገብተው መጥለፍ ጀምረዋል፡፡…›› ብለዋል፡፡  ጉዳት ስለደረሰባቸው ኢትዮጵያዊያን ሲናገሩም  መሀመድ ስለተባለ ልጅ ‹‹..አስረውት በጣም አሰቃዩት፡፡ ከየትም ይሁን ገንዘብ አስልክ ብለው ደበደቡት፡፡ በገመድ አስረው ብረት ላይ ሰቅለው ተጫወቱበት፡፡ መኪና ላይ አስረው መሬት ለመሬት ሲጎትቱት ራሱን ስቶ ሲወድቅ እጁ ከክንዱ ተላቆ ከጥቅም ውጭ ሆነ፡፡…››  ሌላኛው ከአጋቾች እጅ የወጣ ስለጓደኛው የተናገረውን ሲገልጹ ‹‹…ራቁቱን አስተኝተው ሲጋራ ላዩ ላይ እየተረኮሱ ስስ ብልቱን በእሳት እያቃጠሉ ሲጫወቱበት ቆይተው ገደሉት፡፡ ሬሳውን አውጥተው የት እንደጣሉት አይታወቅም፡፡
   አሁን ነጻ ካወጧቸው መካከል 3 ሰዎች ተገለዋል፡፡ 8 የባንግላዲሽ ዜጋዎች ጠፍተዋል፡፡.. በማለት ለጋዜጠኛው ቃል ሰጥተዋል፡፡
      ይህ በዚህ ሁኔታ እያለ ስራ ቦታዬ ሱቅ ውስጥ ተሰባስበን ምሳ ስንበላ ብስቁል ያለ እና የጠቋቆረ ልጅ ርቦኛል የሚበላ ነገር ካላችሁ የሚል ምልክት አሳየን፡፡ አብሮን እንዲበላ ብንጋብዘውም ቅስስ ያለ እና ከእኛ ጋር ተሻምቶ ሊበላ የማይችል በመሆኑ ቀንሰን ሰጠነው፡፡ አማርኛ ብዙም አይችልም፡፡ የሐረርጌ ጭሮ አካባቢ ልጅ ነው፡፡ ሀሰን አልዬ ይባላል፡፡ በደረሰበት ድብደባ ቅስስ ማለት ብቻ ሳይሆን እንደ ወር ጎመን ጥውልግ ልሙስሙስ ብሏል፡፡ ሁኔታው አንጀት ይበላል፡፡ አናቱ ላይ በደረሰበት ድብደባ ችግር የተከሰተበትም ይመስላል፡፡ ተበርቅሶ የተሰፋበት ትልቅ ጠባሳ በጉልህ ይታያል፡፡ አብረን ምሳ ስንበላ ከነበርነው ውስጥ ሙራድ አብዱራህማን የጅማ ልጅ በመሆኑ ኦሮምኛውን በማስተርጎም በኩል ረዳኝ እና አወራን፡፡ ራሱን የቻለ አሳዛኝ ምዕራፍ ስለሆነ ቀጥሎ ልመለስበት አሰብኩ፡፡
Posted by Hellen Tesfaye
Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s