ጸረ ሙስና ከ8 ሚሊዮን ብር በላይ የተዘረፈ ገንዘብ እና ሌሎች ንብረቶችን ወረሰ

ኢሳት ዜና:-የፌደራልየሥነምግባር እና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን በ2005 በጀት ዓመት ዘጠኝ ወራት ውስጥ በሙሰኞች የተመዘበረ
ከ8ሚሊዮን ብር በላይ ጥሬ ገንዘብ፣ መሬት፣ ህንፃዎችና ሌሎች የተለያዩ ንብረቶችን ለመንግሥት ማስመለሱን
አስታወቀ፡፡
ኮሚሽኑ ከሐምሌ 1 ቀን 2004 ዓ.ም እስከ መጋቢት 30 ቀን 2005 ዓ.ም ባሉት ጊዜያት ብቻ በሙሰኞች
የተመዘበሩ 8, ሚሊዮን 11 ሺ 710 ብር በጥሬ ገንዘብ ፣ 1 ሺ 945 ካ/ሜ መሬት ፣ 3 የዝሆን ጥርሶች፣ 1 የተጠናቀቀ
እና 3 በግንባታ ላይ ያሉ በድምሩ አራት ህንጻዎችን፣ ግምታቸው  195 ሺ 000 የሆነ 23 ብላክቤሪ የሞባይል
ቀፎ እና ሌሎችንም ለመንግስት ገቢ እንዲሆኑ ማስደረጉን ገልጿል።

በዘጠኝ ወሩ በፍ/ቤት 23 የንብረት ክርክሮች ውሳኔ ያገኙ ሲሆን ኮሚሽኑ ሁሉንም ክርክሮች መርታት በመቻሉ አፈጻጸሙ 100 በመቶ መሆኑ ታውቋል፡፡ በተጨማሪም ከተጠርጣሪዎች ንብረት ማሳገድ ጋር በተያያዘ 4 ሺ 770 ካ/ሜ መሬት፣ 22 ተሸከርካሪዎች፣ 59 የመኖሪያ ቤቶች ፣ 8 ድርጅት፣ 3, ሚሊዮን 12 ሺ 332 ብር  በጥሬ ገንዘብ እንዲታገዱ መደረጉን ገልጿል፡፡
ከምርመራና ክስ ስራ ጋር በተያያዘ በዘጠኝ ወራት 2 ሺ 761ጥቆማዎችን ለመቀበል የተቻለ ሲሆን ከእነዚህ ጥቆማዎች፣
አቤቱታዎችና መረጃዎች መካከል በኮሚሽኑ የሥልጣን ክልል ስር የሆኑት 1 ሺ 215  ሲሆኑ ቀሪዎቹ
1,546  በኮሚሽኑ ሥልጣን ሥር የማይወድቁ ሆነው ተገኝተዋል ብሎአል።
በተጠቀሰው ጊዜ ምርመራቸው የተጠናቀቀ መዝገቦች ብዛት 339 እና የፍርድ ውሳኔ የተሰጠባቸው መዝገቦች ብዛት
164 ሲሆን ከነዚህ ውስጥ ኮሚሽኑ የረታባቸው መዝገቦች ብዛት 144፣ የፍርድ ውሳኔ ያገኙ ተከሳሾች ብዛት
ደግሞ 409 መሆኑ በሪፖርቱ ላይ ቀርቧል፡፡

የፍርድ ውሳኔ ካገኙት ተከሳሾች መካከል 293 ተከሳሾች የጥፋተኝነት ውሳኔ የተላለፈባቸው ሲሆኑ በዚህ መሠረት የኮሚሽኑ በፍርድ ቤት ጥፋተኛ የማሰኘት ምጣኔ በመዝገብ 88 በመቶ ሲሆን በተከሳሽ ደግሞ 72 በመቶ መሆኑም ከኮምሽኑ የተገኘ መረጃ ይጠቁማል፡፡
በተያያዘ ዜና ኮምሽኑ የሐብት ምዝገባ ያካሄደባቸውን ከፍተኛ ባለስልጣናት በትክክል ያላቸውን ሐብትና ንብረት
ለሕዝብ ይፋ እንደሚያደርግ በሕግ ቢደነገግም እስካሁን ግን የኮምሽኑ ሹማምንት ይህን መረጃ ይፋ ለማድረግ
ከመፍራታቸው ጋር ተያይዞ ዝምታ መንገሱ ታውቋል፡፡
መጋቢት 12 ቀን 2002 ዓ.ም በፓርላማ የጸደቀው የባለስልጣናትና ተሿሚዎች ሃብት ማሳወቂያና ማስመዝገቢያ አዋጅ
ቁጥር 668/2002 ከወጣ በኋላ በ2003 ዓ.ም የሃብት ምዝገባ ስራው የተጀመረ ሲሆን በዚያው ዓመት እስከሰኔ
30/2003 ዓ.ም ባሉት ጊዜያት ብቻ የቀድሞ ጠ/ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ ጨምሮ ፕሬዚዳንት ግርማ
ወ/ጊዮርጊስ፣ የፓርላማና የፌዴሬሽን ም/ቤት አባላት፣ሚኒስትሮች፣ሚኒስትር ዴኤታዎች፣የፌዴራል ፖሊስና የመከላከያ
ከፍተኛ ሹማምንት፣የገቢዎችና ጉምሩክ ከፍተኛ ኃላፊዎች፣የአዲስአበባ አስተዳደር ተሿሚዎችና የመሳሰሉትን
የተካተቱበት በድምሩ 17 ሺ 555 ሰዎች ሃብታቸውን ማስመዝገባቸውንና ቀሪዎችንም የመመዝገብ ስራ እስካሁን መቀጠሉን
ከኮምሽኑ የተገኘ መረጃ ያመለክታል።
በርካታ ከፍተኛ ባለስልጣናት ከገቢያቸው በላይ የተንደላቀቀ ህይወት እንደሚመሩ የሚገመት ሲሆን ኮምሽኑ
የእያንዳንዱን ባለስልጣን የሃብት ምዝገባ ፋይል ለሕዝብ ይፋ ሲያደርግ ማን ምን አለኝ ብሎ እንዳስመዘገበ፣ማን
እንደደበቀ በግልጽ የሚታወቅ በመሆኑ ይህን ስራ ለማከናወን ቁርጠኛ አቋም ሊይዝ አለመቻሉን ምንጮቻችን
ጠቅሰዋል፡፡

እንደ አዋጁ ድንጋጌ ኮምሽኑ ምዝገባውን ለሕዝብ ይፋ ካደረገ በኋላ ማንኛውም መረጃ ያለው
ሰው እገሌ በትክክል አላስመዘገበም በሚል ጥቆማ ማቅረብ እንደሚችልና ይህ ትክክል ከሆነም ባለስልጣኑ ወይም
ተሿሚው በሕግ ጭምር ይጠየቃሉ፡፡

የኮምሽኑ ኃላፊዎች ይህን ጉዳይ አስመልክቶ በቅርቡ መረጃው ይፋ ይሆናል የሚሉ መግለጫዎችን በመንግስት መገናኛ ብዙሃን በተደጋጋሚ ከማውጣት ውጪ ስራውን ደፍረው ሊያከናውኑ እንዳልቻሉ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች አረጋግጠዋል፡፡

Posted by Hellen Tesfaye

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s