የሚያዝያ 30 ማስታወሻ

(ከአገቱኒ መጽሐፍ የተቀነጨበ)

ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማሪያም

 

በአሥራ ስምንት ዓመታት የማታለልና የባዶ ተስፋ ውርጅብኝ ውስጥ ማንም ያላሰበውና ማንም ያልጠበቀው ጥሩ ፍሬ በቀለ! ቅንጅት የተለፈፈውን እንከን የሌለበት የሚል ውሸት አመነና ተቀበለ፤ ይህንን ውሸት ሕዝቡም እንዲያምን አደረገ፤ ‹‹ይታያል ጉዱ!›› ብሎ በሙሉ ልብ ተነሣ፤ ውሸቱን በቅን መንፈስ እንደእውነት ተቀበለው፤ ሚያዝያ 30 የዚህ በቅን መንፈስ የመታለል ብሥራት ነው፤ ለሰላም፣ ለፍትሕ፣ ለነጻነት፣ ለሥልጣን ባለቤትነትና ለአገር ኩራት የኢትዮጵያ ሕዝብ ያለውን ጽኑ እምነት የወያኔን የማታለል ልማድ ፊት-ለፊት በገሀድ የገጠመበት ነው፤ ስለዚህም የወያኔን አታላይነት እርቃኑን ያወጣበት ታሪካዊ ቀን ነው፡፡Prof. Mesfin Woldemariam

 

ቀደም ብሎ ቅንጅት ለሚያዝያ 3ዐ ሕዝባዊ ስብሰባ በመስቀል አደባባይ እንደሚደረግ አሳውቆ ነበር፤ ስለዚህም ሚያዝያ 29 ቀን 1997 ወያኔ/ኢሕአዴግ በመስቀል አደባባይ ሕዝባዊ ስብሰባ ጠራ፤ በሺህ የሚቆጠሩ የንብ ምልክት ያለባቸው ሹራቦችና ቆቦች ተሰፍተው ለሕዝብ በገፍ ታደሉ፤ ጥሬ ገንዘብም ታድሏል ተብሎ ተወራ፤ የመንግሥት መኪናዎችና አውቶቡሶች በፈቃደኛነትም ይሁን በመደለል ወይም በግዴታ ወደ መስቀል አደባባይ የሚሄደውን ሕዝብ ያመላልሱ ጀመር፤ በአውቶቡሶች ወደ መስቀል አደባባይ ከሚጓዙት ውስጥ አብዛኛዎቹ የወያኔ/ኢሕአዴግን ሹራብ ለብሰው የቅንጅትን ምልክት ያሳዩ ነበር፡፡

 

ለማናቸውም የመስቀል አደባባይ በሕዝብ ሞላ፤አቶ መለስ ዜናዊም በአሥራ አምስት ዓመታት ውስጥ  ምናልባትም ለሦስተኛ ጊዜ በዚያ አደባባይ ተገኝቶ ንግግር አደረገ፤ በጣም ደስ ብሎት ስለነበረ ‹‹ሕዝባዊ ማዕበል›› የሚል ስያሜ ሰጠው፤ የአብዛኛውን ሕዝብ ልባዊ ድጋፍ እንዳገኘ ማረጋገጫ መስሎ ታየው፤ በገንዘብየተደለለንና በጉልበት የተገደደን ሕዝብ ስሜት ለማወቅ ረቀቅ ያለ አስተሳሰብን ይጠይቃል፤ስለዚህም በግርድፉ ብዛትን ብቻ መመዘኛ በማድረግ ሚያዝያ 29 አስጨፈረ፡፡*

 

በነጋታው በሚያዝያ 3ዐ የቅንጅት ሕዝባዊ ስብሰባ በዚያው በመስቀል አደባባይ ከሰዓት በኋላ በስምንት ሰዓት ተጠርቶ ነበር፤ በአምስት ሰዓት ግድም አደባባዩ ብቻ ሳይሆን ከየአቅጣጫው የሚመጡት መንገዶች ሞሉ፤ ከአካባቢው ከተሞች አውቶቡስና መኪናእየተከራዩ መጥተው አዲስ አበባን አጥለቀለቋት፤ አቶ መለስ ቸኩሎ ሕዝባዊ ማዕበል ካለው ከአራት አምስት ጊዜ እጥፍ የሆነ የሕዝብ ቁጥር ነበር፤ ወጣት፣ ሽማግሌ፣ ወንድ፣ ሴት ሳይባል የአዲስ አበባና የአካባቢው ሕዝብ ቤቱን ዘግቶ በነቂስ የወጣ ይመስል ነበር፤ በአዲስ አበባ ዙሪያ ከሚገኙ ከተሞች በአውቶቡስና በሚኒባሶች የሚመጡ ብዙ ሰዎች መንገዶቹ ሁሉ ተዘግተው ስለነበረ አልደረሱም፤ የሚያዝያ ሠላሳው ሕዝባዊ ስብሰባ ዋናው አስደናቂነቱ የሕዝብ ብዛት ብቻ አልነበረም፤ ሰላማዊነቱና ጨዋነቱም የሚያኮራ ነበር፤  በዚህ ረገድ በየትም ቢሆን ታይቶ የማይታወቅ ነበር፤ በሚልዮን የሚቆጠር ሕዝብ ወጥቶ አንድ ቅጠል ሳይበጠስና ምንም ዓይነት ረብሻ ሳይነሣ በሰላምና በፍቅር መበተኑ የማይረሳ ኢትዮጵያዊ ታሪክ ነው፤ ይህ እንዲሆን ቅንጅት ያደረገው ዝግጅትና አስተዋጽኦ ከባድ ነበር፤ በፖሊሶች በኩል የታየው ሥርዓትም በጣም አስደናቂ ነበር፤ ፖሊሶችም እንደቅንጅት ሳይታለሉ አልቀሩም ይመስለኛል፡፡

 

ሚያዝያ 30/97 የመታለል ውጤት ከሆነ ላታለለውም ለታለሎትም ትልቅ ትምህርትን ትቷል፤ ቅንጅት ለሰላም የቆመ ድርጅት መሆኑን አረጋግጧል፤ ሚያዝያ 3ዐ ቀን 1997 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ መጀመሪያውና ወደር የማይገኝለት የሰላማዊ ትግል መግለጫ ሆኖ እንደሚቆይ  አያጠራጥርም፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ገና ነው፤ አያውቅም፤ እያሉ የሚንቁትን ሁሉ በተጨባጭ ያሳፈረበት ቀን ነው፤ ሕጋዊነትንም፣ ጨዋነትንም፣ መብቱንና ግዴታውን ማወቁን በተግባር አሳየ፤ የሚጠቅመውንና የማይጠቅመውን መለየት እንደሚችል በተግባር ገለጠ፤ ወያኔ/ኢሕአዴግ በኋላ ቅንጅትን ጸረ-ሰላምና የጎዳና ነውጥ ቀስቃሽ ለማስመሰል ያደረገውን ጥረት የሚያዝያ ሠላሳው እውነት ገሀድ ማስተባበያ ይሆንበታል፡፡

 

በኋላ ባይበላሽ  ይህ ሕዝባዊ ስብሰባ ወያኔ/ኢሕአዴግንም ሊያስመሰግንና ታሪኩን ሊያደምቅለት የሚችል ነበር፤ በሚልዮን የሚቆጠር ሕዝብ በአካል ተጣብቆ ቆሞ ምንም ዓይነት የስሜት መሻከርና ጠብ ሳይፈጠር በመተባበርና በመደጋገፍ በአንድ በጎ መንፈስ በአንድ ላይ ተጠምዶ በራስ መተማመንን፣ ፍቅርንና ተስፋን ሰንቆ አዲስ የነጻነት ኢትዮጵያን ለመገንባት ያስብ ነበር፤ ይህ ዘላቂ ቢሆን ክብርና ምስጋናው ለወያኔ/ኢሕአዴግ ነበር፤ የወያኔ/ኢሕአዴግ የታሪክ ግንዛቤና የታሪክ ሚዛን ማጣት ወያኔ/ኢሕአዴግን ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያንና የኢትዮጵያ ሕዝብንም አደኸየ፤ በምድረ ኢትዮጵያ ሕዝብ የወሳኝነት ሥልጣን አግኝቶ ራሱ የመረጠውን መንገሥት በመንበር ላይ ለማውጣት የሚችልበትን ሁኔታዎች ሁሉ ፈጠረና መጨረሻውን ለመቀበል ሲደርስ ወኔው ከዳው፤ የኢትዮጵያ ታሪክ ሳይለወጥ ቀረ፤ በዚህም ምክንያት ወያኔ/ኢሕአዴግ የኢትዮጵያ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ደራሲ የመሆን ዕድል አመለጠው፤ የደርግ የባሕርይ ልጅ የሆነ መስሎ ታየ፡፡

 

ሚያዝያ 30 የሚያስደነግጥ እንደነበረም መካድ አይቻልም፤ በተለይ በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ እምነት ለሌለውና ለፍርሃት የተጋለጠ ባሕርይ ላለው፣ ጸጥ ያለውንና የረጋውን ባሕር አንደማእበል ለሚመለከተው አስፈሪ ነበር፤ አስፈሪነቱ ግን ከሕዝቡ ሳይሆን ከፈሪው ልብ የመመነጭ ነበር፤ ለወያኔ/ኢሕአዴግ ሚያዝያ 3ዐ የፍርሃትና የመርበድበድ፣ የመደናበርና የመደናገጥ መነሻ ሆነባቸው፤ የአዲስ አበባ ሕዝብ ከሱም ጋር መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ወያኔ/ኢሕአዴግን በሰላማዊ መንገድ ከሥልጣን ለማውረድ ቁርጠኛ ውሳኔ ማድረጉን በማያወላውል መንገድ ለወያኔ/ኢሕአዴግ በገሀድ አሳወቀ፤ ወያኔ/ኢሕአዴግም በበኩሉ ያደረበት ድንጋጤ ድሮውንም ያልነበረውን የማሰብ ችሎታ አጠፋበት፤ ስለዚህም ‹‹እንከን የለሽ ምርጫ›› በማለት የገባውን ቃል ተከትሎ  የተጀመረውን ሕጋዊና ሰላማዊ  መንገድ በአንድ ጊዜ ቀልብሶ  ወደ ሕገ አራዊት የጉልበት እርምጃ የመሸጋገር ምልክቶች ታዩበት፤ በየገጠሩ የቅንጅት አባሎችን ማዋከብ ማሰርና ማጉላላት፣ አልፎ አልፎም መግደል  ዋና የወያኔ/ኢሕአዴግሎሌዎች  ተግባር ሆነ፤ የቅንጅትን የጣት ምልክት ማሳየት እንደክፉ ወረርሽኝ ይታይ ጀመር፤ ጣቱን የተቆረጠም ነበር ሲባል ሰምቻለሁ፡፡

 

በእውነት ከሆነ ለምን የወያኔ መሪዎች ደነገጡ ብሎ የሚገረም ሰው አይኖርም፤ በምርጫው ዘመቻ ጊዜ፣ በክርክሩ ጊዜ ብዙ ሊያስደነብሩዋቸው የሚችሉ ነገሮች ተብለዋል፤ እንትን ያለበት ዝላይ አይችልም እንደሚባለው ቀላሉን ሁሉ እያከረሩ በመተርጎም ራሳቸውን  በፍርሃት አናወጡትና ለመሪነት ብቃት  እንደሌላቸው ለዓለም አሳዩ፡፡

 

ኢትዮጵያ  ለአፍሪካ ብቻ  ሳይሆን ለጥቁር ሕዝብ በሙሉ የነጻነት ጮራ እንደነበረች ሁሉ የዴሞክራሲን  ጮራ  ለማስተጋባት የነበራትን ዕድል ወያኔ መካብ ጀምሮ ወያኔ  ናደው፤ ዓለም በሙሉ በዚህ  እንዲያውቀው መረጠ፤ ቅንጅትም፣ ወያኔም በሚያዝያ 30 ለታሪክ በቁ፡፡

 

—–

* በአፄኃይለ ሥላሴ ዘመን አንድ ለቅሶ ቤት ሁለት ሽማግሌዎች ሲጫወቱ የሰማሁትን ልንገራችሁ፤ አንደኛው የብሥራተ ወንጌል ራድዮ ጣቢያንአንስተው የወሬውን አቀራረብ፣ ትንተናውን፣ አማርኛውን እያወደሱ ተናገሩና ‹የኢትዮጵያ ራድዮ ለምን እንደዚያ አልሆነም?››ብለው በመደነቅ ሲጠይቁ ጓደኛቸው ‹‹አይ ያንተ ነገር! አምነውበት የሚናገሩትና በል ተብለው የሚናገሩት እንዴት እኩልይሆናል?›› አሏቸው፡፡

 Posted by Hellen Tesfaye

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s