ኢትዮጵያዊ ሙስሊሞች ወይስ በኢትዮጵያ የሚኖሩ ሙስሊሞች?

by minilik salsawi

ግንቦት 25/2005 ኢትዮጵያውያን እግረ ሙቁን የሰበሩበት እለት፣ከ8 ዓመታት የዝምታ፣ የጭጭታ፣ የሹክሹክታ፣ የአሉባልታ፣ የፌስቡክ ጫጫታ (ይች እንኳን ገና አድስ ናት) ዘመናት በኋላ ሠማያዊ ፓርቲ ከሠማይ እንደወረደ መና ሆኖ የኢህአዴግን ደርብ ተፈታተነ፣የታፈኑ ድምፆችንም ለነ ጆሮ ለምኔ አስተጋባ፣በኑሮ ውድነት ሆዳቸው የጮኸባቸው ወይም የምንዱባን ጎረቤቶቻቸው የርሃብ ስቅታ የቀሰቀሳቸው ስለ ሆዳቸው ስለ መከራቸው እሪ አሉ፤ሠብዓዊነት ትቢያ ለብሣ ዘረኝነት በወያኔ ዘመን የእርከሰት ጥግ ደረሰችና ከጎጤ ውጣ፣ከቀጠናዬ አልይህ የልማታዊነት ክብር በሆነበት ዘመን ይህ ያልተዋጠላቸው ብቻ ሣይሆኑ እግረ ሙቁን ለመፍታት ወኔ ያላቸው ስለ አጥንትና የደም-ሐረግ ሣይሆን ስለ ሠብዓዊነት “እሪ!!!” አሉ፡፡ የዚህ ታሪካዊ ትዕይነተ-ህዝብ ሌሎቹ ፈርጦች ደግሞ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ናቸው፣አዲስ አበቤዎቹ ሙስሊሞች የዳበረ የሰልፍ ተሞክሯቸውን ለሌሎች ወንድሞቻቸው ማካፈላቸው ለሰልፉ ሠላማዊነት የራሱን አስተዋፅኦ አበርክቷል፡፡ በዚህ ሰልፍ ላይ ሙስሊሞች በዝተዋል የሚል ጉንጭ አልፋ ወግ ጠራቂዎችን ሰምቻለሁ፡፡ አዎ! የአፈና ብረቱን ቀድመው ሰብረውታልና፣የሶስት መንፈቅ የአደባባይ ልምድ አላቸውና፣የኢትዮጵያ ውድመት እንቅልፍ ይነሣቸዋልና ከወንድሞቻቸው ጋር ነፃነትን ሊሹ በሰማያዊ ፓርቲም ላይ ተገኝተዋል፡፡ ኢህአደግም ይህንኑ የአመለካከት ዝቅጠት በሰፊው አስተጋብቶታል፡፡የሙስሊሞቹ በብዛት መገኘት፣የታሰሩ የህዝበ ሙስሊሙ የመፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴዎች አጀንዳ መሆናቸው፣የነዚሁ ግዞተኞች ጠበቃ የሆኑት ዶ/ር ያዕቆብ በሰልፉ መገኘት፣በመጨረሻም ህዝበ ሙስሊሙ የዝሁር ሶላትን ከአማረ ቁኑት ጋር መስገዱን የሰልፉ ነውሮች አድርጎ አቅርቧቸዋል፡፡ ይህ አስተሳሰብ የሚመነጨው “በኢትዮጵያውያን የሚኖሩ ሙስሊሞች” ከሚል ውርደት ነው፡፡ እኛ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ዛሬ ዜግነት የምንለምንበት ዘመን ላይ አለመሆናችንን እኮ የዛሬ አመት ቀድመን አሳውቀናችሁ ነበር፡፡ “በኢትዮጵያ ጉዳይ ሙስሊሞች አያገባቸውም፤በሙስሊሞች ጉዳይም ኢትዮጵያውያን አያገባቸውም!” የሚለውን አፄያዊ ብሒል ለመሰረዝ አበው ብርቱ ትግል አድርገውበታል!

*አንድ ነው ደማችን ከወንድሞቻቸን
ተባብረን እንገስግስ ከገዛ ህዝባችን!!*

ሲሉ እኮ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞችና ክርስቲያን ወንድሞቻቸው በታላቁ የ1964ቱ ሠልፍ ላይ የእስላም አገሩ መካ የወፍ አገሩ ወርካ!ን ብሒል ለአንደዬና ለመጨረሻ ጊዜ ሞግተው ነበር!! ከሠልፍ በኋላም ይህ ጥያቄ ላይነሣ አምባገነኑ ደርግ እንኳን መልስ የሠጠበት ጉዳይ ሆኖ ያለፈ መስሎን ነበር! ለካስ ይህ የነቀዘ-ቀኖና ዳግም በወያኔና ጀሌዎቹ ቤተ-መንግስት መጋበዙን በግንቦት 25 ና 26 ምሽት ኢቲቪ አርድቶናል! እኔም እላለሁ ይህ ትውልድ ዜግነቱን ከማንም አይለምንም!! “ፓለቲካና ሐይማኖት የማይገናኙ ናቸው” ያሉት አቶ ሽምላስና ሬድዋን ከ18ኛው ክፍለ ዘመን ቅዠታቸው አሁንም አልነቁም! የዛሬ ትውልድ ሙስሊም እኮ እየጠየቀ ያለው የፓለቲካ ጥያቄ ነው! የስልጣን አይደለም እንጅ! የኢህአዴግ የአፍ ሣይሆን የአመለካከት ወለምታ የመነጨው አንድም በኢህአዴግ አስተሳሰብ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች በ18ኛው ክ/ዘመን የንቃተ ህሌና እርከን ውሥጥ እንዳሉ ከማሰብ የሚመነጭ ነው፣ሁለትም በኢህአዴግ መዝገበ ቃላት መንግስትና ፓለቲካ ፣ሐገርና ፓርቲ ፣መንግስትና ፓርቲ ልዩነት አለመኖራቸው ነው፡፡ “ሠማይ አይታረስ መንግስት አይከሰስ!” ዛሬም ህያው መሆኗን አቶ ሽመልስና ሬድዋን እያረዱን ይገኛሉ! በህግ-የበላይነት አፈፃፀምና በፍርድ ቤቱ ነፃነት ላይ ጥርጣሬን የቋጠረ ህዝብ ድምፁን የት ሂዶ እንዲያሰማ ነው ኢህአዴግ እየፈለገ ያለው? ኢህአዴግን ልንከስ እንጅ ለናመሰግን አለመውጣታችንን ሊረዱ ይገባ ነበር ሠማያዊ ፓርቲ ሠልፉን ላልተፈለገ ዓላማ አውሎታል ከማለታቸው በፊት!
ኢትዮጵያውያን በ1997 ኢትዮጵያን ከዘውጋዊ መሣፍንት ነጻ ሊያወጡ ቴዎድሮስን ሆነው ብዙ ደከሙ መጨረሻም ቴዎድሮስ መቀደላ እንደተረቱት ሁሉ ኢትዮጵያውያንም በድምፅ ኮሮጃ ውስጥ በተሰራ ሸፍጥ ሳቢያ በመጣው ሁከት ድል ተነሱና ተስፋ ቆረጡ፣አፄ ቴዎድሮስም ኢትዮጵያን አንድ ሊያደርጉ የሞከሩት ሙከራ ሁሉ በኢትዮጵያውያኑ ሴራ አልሳካላቸው ቢል እንዲህ ሲሉ ተቀኙ፡

*እኔ ምን አገባኝ ቢበስል ባይበስል
ገና ሆዴ ሽሮ ይበላ ይመስል! *

የዛሬው ትውልድም በኢህአዴግ በትር ተስፋ ቆርጦ ይህችን የቴዎድሮስ ውርስ በየቤቱ እየተቃኘ ድፍን ስምንት አመታትን ባስቆጠረ ማግስት ነው እንግዲህ ሠማያዊዎቹ በአገር ጉዳይ እኔ ምን አገባኝ አይባልም ያሉት፣ሠልፈኞቹም በሐይማኖት ጉዳይም እኔ ምን አገባኝ አይባልም ሲሉ ተስፋ መቁረጥና ፍርሃት የወለደውን “ምን አገባኝ!” ሊገዳደሩ አደባባይ የዋሉት! ታዲያ እኛም አላሳፈርናቸውም በደርግ ጊዜ ለአቢዮት ታጋዮች በተገነባው የትግላችን ሐውልት ፊት ለፊት አንዲም ታግለንበት ሁለትም ሰግደንበት ኢህአዴግን ሆድ አስብሰነው በሠላም ወደየቤታችን እፍ አልንበት! በእርግጥ መጀመሪያ ፍትህ እያሉ ቃሊቲ ገቡ! ብለን ዘምረናል! የውሸት ህንፃን በሩቁ ባየንም ጊዜ “ኢቲቪ ሌባ፣ዛሚ አቃጣሪ!” ብለናል፡፡
የኢትዮጵያ ዙፋን ላይ የወጣ ሁሉ፣ጭቃ ሹም፣ምስለኔ በተነኮሰው ቁጥር ታግዮ መብቴን አስከብራለሁ ከማለት ይልቅ

*ለዋንዛ ብነግረው ነገረው ለዋርካ*
*አልሐምዱሊላሒ እሄዳላሁ መካ!*

እያለ አረብ አገራትንና ቆላን መደበቂያ የሚያደርገው ትውልድ ዛሬ የለም! መቼም ይች ግጥም በልጅነታችን በአጋም እሾህ ከቤታችን ግድግዳ ላይ እንደተሰቀለች ቤት ይቁጠረው! ይህ ዜግነትን እንደ መብት ሣይሆን እንደ ስጦታ ከመመልከት የመነጨ ሽሽት በዚህ ዘመን የማይታሰብም የማይሞከርም ሆኗል፡፡ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ከዚህ በኋላ ፓለቲካን የሚፈሩበት ዘመን ማብቃቱን ኢህአዴጋውያን ያወቁ አይመስለኝም! ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞችና ፓለቲክስ የሁለት ዓለም ክሰተት መሆናቸው ያከተመው እኮ መጅሊስ የሚባለው የኢህአዴግ ክንፍ ወደ ትክክለኛው ማንነቱ ይመለስ ዘንድ ነፃና ፍትሐዊ የሆነ ምርጫ በየመስጅዶቻችን እንመረጥ፤ግራ ክንፎቹም ይወገዱ ያልን እለት ነው፡፡ እኔ ከብቶቼን ላርባ ወንበሩ የናንተነው የሚል ሶማሊያዊ እንግዲህ ሊኖር አይችልም፣እኔ የመርካቶ ችርቻሮየን ልቸርችርበት ግብር ብቻ ጠይቁኝ የሚል ስልጢ እንግዲህ አይኖርም! የከፈለው ግብር ለኢትዮጵያውያን ጥቅም ላይ መዋሉን ሣያረጋግጥ ቤቱ የሚገባ ትውልድ እንግዲህ ሊኖር አይችልም! ይህች አገር የኛም ናትና! ስለሙስሊሙ መብት ብቻ ሣይሆን ስለ ዋቄፈታውም፣ስለ ክርስቲያኑም መብት እሪ! ከማለት አልፈንም እንጮኃለን! ኢትዮጵያችን በፍትህ እጦት ስትታመስ ከኢህአዴግም በፊት ኢትዮጵያን አኩርተው ያኖሩ ኢትዮጵያውያን የአንድነታቸው ቋጠሮ በዞምቢዎቹ ተንኮል ሲፈታ፣ዘርና አጥንት የአድዋን ክብር ሲበይኑ እያየን ዝምታን አንመርጥም!! አዎ! በሰልፉም ላይ ኢትዮጵያችንን በእኩይ የደፈረን ሁሉ ይወድም ዘንድ የጥላሁንን ሀገራዊ ሙዚቃም ሞዝቀናል!
*ተከብረሽ የኖርሽው በአባባቶቻችን በአባቶቻችን ደም!*
*እናት ኢትዮጵያ የደፈረሽ ይውድም! የደፈረሽ ይውደም!*
መካን አንድም እንደ ዚያራ ሁለትም እንደ ሒጅራ ይቆጥር የነበረው ህዝብ ዛሬ ደግሞ እንዲህ እያለ ማንጎርጎሩ አይቀርም፡

*አልሐምዱሊላሒ አውቃለሁ መብቴን*
*እወድቅላታለሁ ሐገሬና እምነቴን!*

ኢትዮጵያ የምትባለው አገር የሙስሊሞችና ክርስቲያኖች፣አይሁዶችና ወቄፈታዎች ድምር ናትና ሰልፍ ካለ፣ሆድ የባሰው፣መብቱ የተገፋ፣አንገቱ በቀንበር የተደፋ ሁሉ ኧረ እሪ ሲል ለአምላኩም፣ለጆሮ ለምኔዎችም ስሞታውን ማሰማቱ አይቀርም! እናም ሰልፎች የነዚህ እምነትና ሐይማኖቶች ተከታይ ስብጥር መሆኑ ግድ ይላል። ከአራት ሠዓታት የሠማያዊ ፓርቲ የትዕይንት ቆይታ ውስጥ የባንድራ ድራማን፣የ5 ደቂቃ ስግደትንና ከሙስሊሙ ጋር የሚገናኙ ጉዳዮችን ነቅሶ እንደ ነውር ማውጣትን ምን ማለት ነው? ኢህአዴግ ሠማያዊ ፓርቲን የአሸባሪ ሙስሊሞች ፓርቲ አድርጎ ለማቅረብ እየጣረ ይገኛል፡፡ሠልፉንም ሠማያዊ ፓርቲ ላልተፈለገ ዓላማ አውሎታል እያለን ነው፡፡ አዎ! ኢህአዴግ ለማይፈልገው ዓላማ እንጅ እሡ ለፈለገው ዓላማ ወትሮስ እንዴትና መቼ ወጣንና! በአርግጥ ኢህአዴግ በሚፈልገው ሁኔታ በየቦታው እየተሠለፍንለት አይደል እንዴ ጎበዝ! ለታክሲ እንሠለፋለን፣ባንክ ቤት እንሠለፋለን፣ዳቦ ቤት፣ገቢዎች፣ውሐና መብራት ክፍያ፣ቀበሌ ምን የማንሠለፍበት ቦታ አለ ጎበዝ? ጎበዝ መድረክም፣ኢደፓም….ሁሉም ሰሞኑን ደግሞ በደገሙኝ አላሳፍራቸውም ነበር፡፡መቼም ይህ ሠልፍ ለጆሮ ለምኔው ኢህአዴግ ማስጠንቀቂያ ነው፡፡ኢብን ተይሚያህ አል-ሐበሽይ

 

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s