“ትውልድ ያናወጠ ጦርነት”

ከመጻሕፍት አምባ: “ትውልድ ያናወጠ ጦርነት” (ቅኝት በአበራ ለማ)

June 11, 2013

Click here for PDF

የመጽሐፉ ርእስ……………… ትውልድ ያናወጠ ጦርነት
ደራሲ……………………………. ንጋቱ ቦጋለ (ሻለቃ)
አሳታሚ…………………………. በግል
አታሚ……………………………. ኢንተርናሽናል ሊደርሺፕ የሕትመት ሥራ
የገጽ ብዛት………………………. 341
ዋጋ…………………………………. 55 ብር
ቅኝት………………………………. በአበራ ለማ

ከደራሲው የጦር ሰው የደረሰ ጦማር

ለወንድሜ አበራ ለማ ከሁሉ አስቀድሜ የማክበር ሰላምታዬን አቀርባለሁ።

”የወገን ጦር ትዝታዬ” በሚለዉ የሻለቃ ማሞ ለማ መጽሃፍ ላይ ያቀረብከዉን የመጽሃፍ ግምገማ ጊዜ ወስጄ አነበብኩ ። ከሁሉም በላይ የሰራዊቱን ኑሮና ትግል ደስታና (ደስታ ከነበረ) መከራ አሳምረህ የምታዉቅ መሆንህን በመገንዘቤ በጣም ነው ደስ ያለኝ። የሚያስደንቀዉ ነገር በመስክ ላይ በስራ ላይ ሆነህ የሚሳየዉን ፎቶ ስመለከት አዲስ አልሆንክብኝም። በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ እንተዋወቃለን ብዬ አሰብኩ። ለነገሩ ከዚህ በላይ መተዋወቅስ ምን ፍይዳ አለዉ? ብዙ የምናዉቃቸዉ እንዳማናዉቃቸዉ ሆነዉ በመገኘታቸዉ ምነዉ ባለወቅናቸዉ አሰኝተዉናልና ነዉ።

ወድ አበራ !… የኔንም ሆነ የሌሎች መኮንኖችና ወታደሮችን የጦር ሜዳ ዉሎ መጽሃፍት ተከታትለህ ማንበብህ አልደነቀኝም። የስነ ጽሁፍ ሰዉ መሆንህ ብቻ ሳይሆን ታሪክ እያለዉ እንደሌለዉ ለሆነዉ፤ ጀግና እንዳልነበረ ሁሉ ፈሪ ተደርጎ ስለተፈረጀዉ፤ ለሀገሩ አንድነትና ዳርድንበር መከበር ለዓመታት መስዋትነት ክፍሎ ሳለ ጨፍጫፊ ተብሎ ተፈርጆና ተረግሞ ስለቀረዉ ሰራዊት ማንነት የምታዉቅ ብቻ ሳትሆን ኑሮዎን አብረህ የኖርክ የታሪክ ምስክር፤ በመሆንህ ጭምር ነዉ ። በድጋሚ ላመሰግንህ እወዳለሁ።

በእኔ አስተያየት የሰጠኽዉ ግምግማ ወደፊትም ለሚጽፉት ሶዎች ትልቅ ትምህርት የሚሆን በመሆኑ በተገኘዉ መገናኛ ብዙሃን ሁሉ ቢለቀቅ መልካም ነዉ እላለሁ፡፡ በዚህ አጭር ጽሁፍ ዉስጥ መቼም የማላገኘዉ ትምህርት እንደተማርኩ ልነግርህ እወዳለሁ። ፍርሃትም ድፍረትም ሰጥቶኛል ። ግምገማህን ካነበብኩ በኋላ የፈራሁት አንተን የመሰሉ የስነጽሑፍ ሰዎች ያነበቡትን መጽሃፍ ጽፌ ለንባብ ባበቃም፣ ምን ያህል ገና እንደሆንኩና ምንስ ያህል ብዙ እንደሚቀረኝ እያሰብኩ ነዉ። ሰዉ አለማወቁን የበለጠ ሲያዉቅ ይፈራልም ይተጋልም። በሌላ በኩል ድፍረት የሰጠኝ ተግቼ እንድሰራ ግምገማህ የበለጠ የሚያበረታታኝ መሆኑ ነዉ። ለዚህ ነዉ ሁለቱንም ሆንኩ ያልኩህ።
ጊዜ ብታገኝ የእኔንም መጻፍ ብትገመግመው ደስታዉን አልችለዉም።

ሙያህን እግዚአብሄር ይባርክ
ወንድምህ ንጋቱ ቦጋለ (ሻለቃ)

New Amharic book "tewled yanate tornet"

ይድረስ ለወንድም ጓዴ ሻለቃ ንጋቱ

ሰላምታዬ ታለሁበት የሰሜን ዋልታ ግርጌ ይድረስህ፡፡ የጻፍክልኝ ኮርኳሪ ጦማር ደርሳኝ አጣጥሜያታለሁ፡፡ እግዚአብሄር ይስጥልኝ፡፡ አበርክቶም የብእር በረከቱን ያብዛልህ፡፡ አንተ የውትድርናው አለም ሰው ሁነህ፣ እኔ ደሞ የሲቪሉ ሕብረተሰብ አካል ሁኜ፣ ባንድ ዘመን፣ ባንድ ወቅት፣ ባንድ ትውልድ ሰማይ ስር… ለዚያ ሕይወቱን ገብሮ የሌሎችን ሕይወት ለመታደግ ለተሰማራ ዳር ድምበር አስከባሪ፣ ሉአላዊነትን ታዳጊ ጀግና ጦር ዘምረናል፡፡ የኔ እንኳን እግር የጣለው መንገደኛ ውሎ ያህል የሚቆጠር እንጂ ተፋይዳ የሚገባ አይደለም፡፡ ያንተውና የመሰሎችህ የጀግንነት ውሎ፣ መስዋእትነት፣ ያገራዊ ቃል ኪዳን ጥበቃና ቆራጥነት ግን ወደር አቻ የማይገኝለት ነው፡፡

Abera Lema, Author1ውድ ወንድሜ ንጋቱ፣ ስንቱን አንበሳ እንደወጣ ያስቀረውን ያንን አሰቃቂ የትውልድ ጦርነት በሸጋው ብእርህ አሳምረህ ቀርጸህዋል፡፡Abera Lema, Author2 ከምስራቅ እስከ ሰሜን ጦር ግምባር እያጓጓዝከን በብእር ካሜራህ አስቃኝተህናል፡፡ ያንን ያንድ ትውልድ መንትዮች ወንድማማቾች የተራረዱበትን ያልጌናን ግምባር እልቂት እንደ ሻለቃ ማሞ ”የወገን ጦር ተዝታዬ” መጽሃፍ ሁሉ፣ አንተም ”ትውልድ ያናወጠ ጦርነት” በተሰኘው አዲስ መጽሃፍህ አማካኝነት ፍንትው አድርገህ አቅርበህዋል፡፡

ኤርትራ ውስጥ ከተራራው ክፍል ጦር ጋር የነበረህ ትስስርና ያርበኝነት ቁርኝትህ፣ ካንድ ወታደራዊ ሀቀኛ የፖለቲካ ካድሬ የሚጠበቀውን ግብርህን የፈጸምክበት ምእራፍ ሁኖ ጦር ጋር የነበረህ ትስስርና ያርበኝነት ቁርኝትህ፣ ካንድ ወታደራዊ ሀቀኛ የፖለቲካ ካድሬ የሚጠበቀውን ግብርህን የፈጸምክበት ምእራፍ ሁኖ አግኝቼዋለሁ፡፡ የትናንቱ የኤርትራ የጦር አውድማዎች ውሎ የታሪክ አሻራ ደብዝዞ ያለያም እስከ ማእዜኑ ጠፍቶ እንዳይቀር፣ ያንተ ዓይነቱ የግለ ሕይወት ማስታወሻ ሥራዎች ትልቅ አስተዋጽኦ አላቸው፡፡

ይህ ያንተው የበኩር ሥራ የሆነው “ትውልድ ያናወጠ ጦርነት” በትግራይ ውስጥ የነበረውን እልክ አስጨራሽ ፍልሚያ ባይን ምስክርነትና በባለቤትነት አሳምረህ የቃኘህበት ነው፡፡ የመንግሥት ጦር ከሕወሀት ጋር ያደረገውን አስከፊ ጦርነት ማልደህ ያስተዋልከውን ከግልህ የጦር ሜዳ ውሎ ገጠመኝ ጋር አሰናስለህ ያቀረብክበት ነዉ፡፡ በአድዋ፣ ባክሱም፣ በሃውዜን፣ በሽሬና በትግራይ የተለያዩ አውራጃዎች ውስጥ የተካሄዱትን ውጊያዎች፣ የወገንና የጠላትን አቋም እያነጻጸርክ እንደ ደህና የፊልም ቀራጭ ባለሙያ አሳምረህ አሰናድተህዋል፡፡ አንባቢ ስትውድቅ ወደቆ፣ ስትነሳ ተነስቶ፣ ስትቆስል ቆስሎ፣ ስትራብ ተርቦ፣ ስትጠማ ተጠምቶ አብሮህ ብዙ ብዙ ይጓዛል፡፡ የወያኔ ጦር አይሎ የወገን ጦር አንድ ለስምንት መጋጠም የግድ የሆነበት አስቀያሚ የጦርነት ወሎህ ላይ ያጠነጠንከው ግሩም ትረካህ አይረሴነት ያለው ነው፡፡ የሽሬ አድባር በወገን ውሎ ላይ በስተግራ ተሸርጣ፤ በየፈፋው፣ በየጉድባው፣ በየሸለቆው… ወገንና ጠላትን ለይቶ መዋጋት ያልተቻለበት ያንድ ቤተሰብ ልጆች የርስበርስ እልቂት የታየበት የጦር አውድማ እንደነበር ከግል ማስታወሻህና ተዝቆ ከማያልቅ የክፉ ቀን ትዝታህ አካፍለህናል፡፡

የሽሬ ውጊያ ብሎም በትግራይ ውስጥ የነበረው የመንግሥት ጦር አመራር በነመጋቢ ሃምሳ አለቃ ለገሠ አስፋው ችሎታ ማነስ ምክንያት፣ ምን ያህል ተፍገምግሞ እንደወደቀ ደህና አድርገህ ገልጸህዋል፡፡ መጋቢ ሃምሳ አለቃ ለገሠ አስፋው ጀምለው በያዙት ድርብ ድርብርብ ስልጣን ሳቢያ፣ አንድም የጦር መሪና አዛዥ በራሱ ተነሳሽንት፣ ያለበትን የጦር ሜዳውን ተጨባጭ ሁናቴ እያገናዘበ እንዳይንቀሳቀስ ተቀይዶ እንደነበር ያሰመርክባቸው ነጥቦችህ አንገት የሚያስደፉ ናቸው፡፡ በዚህም ሰበብ የበታቹ የቅርብ አለቆቹ አንዳችም የማዘዝ ኃይል እንደሌላቸው አውቆ ትእዛዝን መቀበል አሻፈረኝ ያለበት አስጠሊታ ሁኔታ ተፈጥሮ እንደነበር ትዝብትህን አካፍለህናል፡፡ ጀነራል ለገሠ አበጀ የጀግናን ገድል ፈጽመው ለጠላት እጃቸውን ላለመስጠት ሲሉ ሽጉጣቸውን ጠጥተው አከሱም ላይ ያሸለቡበትም ምክንያት፤ ይሄው በእዝ ጠገግ ውስጥ አልፎ መደማመጥ የጠፋበት ሥርዓተ አልበኝነት በጦሩ ውስጥ መስፈኑ እንደነበርም ላንባቢያን የሰጠህን ግንዛቤ እውስጣችን የሚኖር ቁስል ነው፡፡ ”በታሪካዊዋ አክሱም እምብርት ላይ መሰዋት ለኔ ኩራቴ ነው” ብለው መሰዋታቸውን የገለጽክበት ድምጸትም እውስጣችን እያንጎራጎርነው የምንኖረው ሰቆቃ ነው፡፡

አስጊ የጤና መታወክ ደርሶባቸው የነበሩት የጀኔራል በረታ ገሞራው አሳዛኝ ፈጻሜም ሌላው ቅስምን የሚሰብር በደል ነው፡፡ ብ. ጀኔራል በረታ ግዙፍ ተክለ ሰውነት ከውስጥ ደዌ ሕመምAbera Lema, Author3 ጋር ተሸክመው፣ እንደልባቸው ተንቀሳቅሰው ለመሥራት ያልተቻላችው ቀን የጎደለባቸው ሰው እንደነበሩ ጥሩ አድርገህ ገልጸሃቸዋል፡፡ በዚሁ በጤና ችግራቸው ምክንያት፣ የ604ኛ ኮር ምክትል አዛዥ ሆነው በተመደቡበት የሽሬ ግንባር ጠቅላይ ሰፈር ውስጥ ከመዋል በስተቀር የረባ ወታደራዊ ግብርን በግንባር ተገኝተው ለመፈጸም እንዳልቻሉም አስታውሰሃል፡፡ ጉዳዩ ያንባቢን ሕሊና ”ለምን?…” በሚል ጥያቄ ሰቅዞ የሚይዝ ነው፡፡ እድሜና ጤና ላንተ ላይን ምስክሩ ይሁንና፣ ጀኔራል በረታ በነሃምሳ አለቃ ለገሠ የሕክምና ፈቃድ ተከልክለው እዚያው ጠቅላይ ሰፈር ውስጥ እየተሰቃዩ እያሉ፣ በጠላት ተከበው መጀመሪያ እግራቸውን በጥይት መመታታቸውንና በኋላም እጠላት እጅ ላይ መውደቃቸውን አርድተህናል፡፡ ያሳዝናል…

ቀደም ሲል ወደ መቀሌ በመሸሽ ያራሳቸውን ደህንነት በመጠበቅ ሕይወታቸውን የታደጉት ለገሠ አስፋውና ጀኔራል ሙላቱ ነጋሽ በተልካሻው አመራራቸው ጦስ የተነሳ ያን ሁሉ ጦር አስጨፍጭፈውና አስማርከው ብቻ እንዳላበቁ ይህ ታሪካዊ መጽሃፍህ ብዙ ብዙ ይለናል፡፡ የ604 ኮር ዋና አዛዥ ጀኔራል አዲስ አግላቸውና ሌላው ቆራጥ አዛዥ ጀኔራል ኃይሉ ከበደ እዋዝ መኪና ውስጥ እንዳሉ በጠላት ላውንቸር ተመተው እንደወጡ መቅረታቸውንና አሳዛኝ ፍጻሜያቸውን ስናስተውል፤ አንድ ሌላ ጥያቄ እውስጣችን ያቃጭላል፡፡ ”ይቺ እናት አገራችን ጀግናን መውለድ እንጂ፣ ጀግናን ማሳደግ ምነው አይሆንላት?” ብለን እንድንጠይቅ ግድ ይለናል፡፡ የትልልቆቹ አንቱ የተሰኙ ጀግኖቻችን ፍጸሜ ሁሉ መጨረሻቸው እንዲህ እንደተማላ ወጥቶ መቅረት… እኛ ቀሪዎቹ ደሞ ታሪካቸውን ቅብርብር… ውለታቸውን ልኩስኩስ… ሲመቸንም በነሱ የመስዋእትነት ገድል ላይ ቆመን እራሳችንን ኩፍስ… መች ይሆን የሕሊና ወቀሳ ግዘፍ ነስቶ፣ ከእኩይ ምግባራችን የምንታረም? ከሀብታችን ይልቅ መልካም ስምን ለልጆቻችን አውርሰን ልናልፍ የምንተጋው?
ወንድም ጓዴ ሻለቃ ንጋቱ፣

የመጽሃፍህን ዝርዝር ፍሬ ነገር ከሀ እስከ ፐ አንስቼ አልዘልቀውም፡፡ አንባቢ ምስክር ይሆነኝ ዘንድ ዋቤ ልጥራ፡፡ ሦስት ነግሮችን ሳላስታውስ ግን ማለፍ አልፈልግም፡፡ አንደኛው የትግራዩ የመንግስት ጦር ”ጥሩ ተሸናፊ” ሁኖ እናንተ በመሸሽ ላይ በነበራችሁበት ሰዓት፣ ጎንደር ውስጥ ጣብላ ሥላሴ ዋሻ ውስጥ ተደብቃቸሁ ሳለ፣ የወያኔ ታጣቂ ኃይል ሲከባቸሁ፣ በፈረደብህ ባንተው ግንባር ቀዳሚነት ከበባውን ጥሳቸሁ ልትወጡ ስትሉ፣ ሙሃይትህ አካባቢ ክፉኛ ቆስለህ ሳለህ ያስጠለሉህ ደግ አባት ገበሬ በውስጤ ተስለው ቀርተዋል፡፡ ስፍራው በጠላት ቁጥጥር ስር በነበረበት በዚያ አስጊ መንደር ሸሽገውህ፤ ያላቸውን እያካፈሉህ፣ ቁስልህን እያጠቡ፣ ከወገኖችህ ጋር እንደምተቀላቅል ልብ የሚሞላ ተስፋ እየመገቡህ ያሰነበቱህን ደግ አባት ዓይነት የጦበያችን አምላክ ያበርክትልን ከማለት ሌላ ምን ማለት የቻላል፡፡ የንዲህ አይነቶቹ የክፉ ቀን ወዳጆች ውለታ እንደምንና እንዴት ተከፍሎ አልቆ የልብ ይደርሳል?… እኛን ደግ አባት ባይጥልልህ ኖሮ ”ነበር” ተብለህ ትታለፍና ትረሳም ነበር፡፡ እኛም አንባቢያን ይህን የመሰለ የመንፈስ ምግብ አግኝተን እንዲህ ባንተ ሥራ ላይ ለመወያየት ባልበቃን ነበር፡፡ እግዜር በጅጉ ይወድሃል፡፡

እኛ አዛውንት፣ እንደክርስቶስ አልባሳት እጣ ተጣጥለውብህ ለጠላት አሳልፈው ሊሰጡህ ከቋመጡት ልጃቸውና ጎረቤታቸው ደባ ከልለውህ የጨረቃ ሌሊት ሙሽራቸው አደርገውህ ወደ ወገኖችህ አሻገሩህ፡፡ በራሳቸው ብቸኛ ፈረስ… በዚያ ግልቢያ በተሳነውና በበቅሎ እስታይል በሚሰግር እድሜ ጠገብ መጓጓዣቸው፡፡ ለመሆኑ እኛ ደግ አባት ዛሬም በሕይወት ይኖሩ ይሆን?… በዘመነ ኢሕአዴግ ለሰባት አመት ተኩል ያህል በእስር ቤት ስትማቅቅ፣ እድል አግኝተህ ልታፈላልጋቸው እንዳልቻልክ ይህን መጽሃፍ ያነበበ ሁሉ ሊረዳው የሚችል ይመስለኛልና ልለፈው፡፡

ሁለተኛው ነጥቤ እስር ቤት በነበርክበት አጀብ ዓመታት ውስጥ የነበረህ የመንፈስ ጠንካሬና ብርታትህ ነው፡፡ ከራስህ ተርፈህ ለሌሎች ተስፋ ላጠጠባቸው የእስር ቤት ጓደኞችህ ታደርግላቸው የነበሩ በጎ ተግባራትና የማጽጽናት ተልእኮህ እልብ ወስጥ የሚቀሩ ናቸው፡፡ ይህንን ያንተን አርቆ አሰተዋይነትና የክፉ ቀን አለኝታነት የመቶ አለቃ በቀለ በላይ በቅርቡ ባጻፈው ”የጀግና ወሮታ” በተሰኘው መጽሃፉ ላይ ጠቅሶ አመሰግኖሃል፡፡ ይሄውም ጦላይና ሆለታ ታስራቸሁ በነበረበት ወቅት ነው የሆነውን ሁሉ አስታውሶ ባወሳበት ምእራፉ ላይ ነው፡፡ እሱ ከሆለታ ሲፈታ አንተ እስርህ ጸንቶብህ ወደ ቃሊቲ መውረድህን ይሄው የሱ መጽሐፍ አሳውቆኛል፡፡ ሰባት ዓመት ተኩል ያለ አንዳች ክስ በወህኒ ቤት ማቀህ በነጻ ስተፈታ፤ ባዶ እጅህን እንዳልወጣህ የጠቀስከው ደሞ ሌላው ጠንካራ የሞራል ጌታ መሆንህን የሚያበስር ነው፡፡ የፈረንሳይኛ ቋንቋንና ሙዚቃን ዓይነት ትምህርቶችን ተመርህ ወጣህ፡፡ በዚህም አላበቃህም፡፡ ከመታሰርህ በፊት በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ጀምረኽው የነበረውን የፖለቲካ ሳይንስ ጥናትህን ቀጥለህ በቢ.ኤ. ድግሪ ለመመረቅ በቅተሃል፡፡ ያውም በዚያኛው ጫፍ እሱ ለወያኔ፣ አንተ ደሞ በሌላኛው ጫፍ ለነበረው መንግሥት ተሰልፋችሁ ስትፋለሙ ከነበርከው ሰው ጋር፣ ባንድ ከፍል ውስጥ ጎን ለጎን ተቀምጣችሁ በጥሩ ወንድማማችነት የመማራቸሁ አስደሳች ዜና አንባቢን በፈገግታ ዘና ያደርጋል፡፡ ታዲያ ከዚህ ሁሉ ጥንካሬህ ጀርባ ከእግዜር በታች እነማን አብረውህ ነበሩ?… ሦስተኛው ነጥቤ እሱ ነው፡፡

ሦስተኛው ነጥቤ የውድ ባለቤትህ የታለም መአዛ ጉዳይ ነው፡፡ ያንተን የመንፈስ ጥንካሬ በሷ ውስጥ፣ የእስዋን ደሞ ባንተ ውስጥ አንባቢ ያያል፡፡ ባልና ሚስት ካንድ ጉድጓድ ይቀዳል የሚለውን አገርኛ ምሳሌ በሰናይ መልኩ ተግብራቸሁት ትታያላቸሁ፡፡ ወይዘሮ መአዛ፣ ቀደም ሲል ትግራይ ውስጥ በዚያ የሞት የሽረት ግዳጅ ላይ እያለህና፤ በኋላም በሰባት ዓመት ተኩሉ የዘመነ ኢሕአዴግ የእስር ዘመንህ ሁሉ በመንፈስና በተግባር ካንተ ጎን አለመለየቷን ብእርህ እያዘከረ ዘምሮላታል፡፡ ሲያንሳት እንጂ ሲበዛባት አይሆንም፡፡ በእስርህ ዘመን እያንዳንዱን ሰንበት ላንተ መድባ ከሆለታና ከቃሊቲ ደጃፍ አልተለየችም፡፡ ብዙም አብራችሁ ለመኖር እድል ያላገኘችው ውድ ባለቤትህ፣ ሳታሰልስ ወህኒ ቤት እየተመላለሰች ሙሽራዋን ለመጎብኘት ጸንታ መቆየቷ የመልካም የትዳር ጓደኛ ተምሳሌት ያደርጋታል፡፡ ዛሬ ወደድኩሽ ወደድኩህ ታባብለው፣ ብዙ ጥሩንባና ፋንፋር አስነፍተው በወሩ ”ጫወታ ፈረሰ፣ ዳቦ ተቆረሰ” ብለው ግምኛ ተለያይተው ለሚቀሩ ጥምሮች ጥሩ ትምህርት የሚሰጥ ነው፡፡ ወይዘሮ መአዛ፣ ባንዲት አነስተኛ ደመወዟ ሕጻናት ልጆቻችሁን እያሳደገች፣ ላንተ ስንቅ እያቀበለች ያን ሁሉ የመከራ ዘመን አሸንፋዋለች፡፡ ይህን ስቅየቷን ተረድተህ፣ በባንክ እዳ የተሠራ ቤታቸሁን (እዳው ተከፍሎ ያላለቀ) እንድትሸጠውና ወጣሪ የቤተሰቡን ችግር እንድትሸፍን ስትጠይቃት፣ የቃሊቲ ጥየቃ ምልልሷንም ከሳምንት ወደ ወር እንድትቀይር ስትጫናት፣ አሻፈረኝ ብላ ባቋሟ ጸንታ መቆየቷን አብስረህናል፡፡ ቤቱንም አልሸጠች፣ ከቃሊቲ የየሳምንቱ ምልልሷም አልታቀበች፡፡ ድንቅ የሕይወት ጓደኛ… ከእንቁም የከበረች!… የሕይወት ቀጣይነት ዋስትና ሰጪ ባለውለታ የሆነች…

ውድ ሻለቃ ንጋቱ… ያንተን ጦማር በዚሁ ልቋጭ፡፡ በርትተህ ሌሎች ገጠመኞችህንም በነካ እጅህ ጀባ ትለን ዘንድ ተስፋዬ ነው፡፡ ዛሬ በምትኖርበት ያማሪካን ምድርምኮ ብዙ የየለቱ ገጠመኝ አለ፡፡ ሸጋው ብእርህ እንደማያንቀላፋ እምነቴ ነው፡፡ አድባርም ትከተልህ… እናም በዚህ አጋጣሚ ወደ ሌላኛው የትግልና የእስር ሕይወትህ ጓድ ሥራ አንባቢዎቼን ይዤ ልሸጋገር…

ሰለባለውለታ ጀግኖቻችን ስናነሳ፣ አንድ በቅርቡ ያነበብኩት መጽሐፍ ጭብጥ ትዝ አለኝ፡፡ የጀግናውን የመቶ አለቃ በቀለ በላይን ”የጀግና ወሮታ” የተሰኘ መጽሃፍ ማንበብ ጥሩ ግንዛቤን የሚያስጨብጥ ነው፡፡ ከሻለቃ ንጋቱ ቦጋለ ጋር የኢሕአዴግ እስረኛ የነበረው የመቶ አለቃ በቀለ በላይ 2ኛ ደረጃ የጦር ሜዳ ጀበዱ ሜዳይ ተሸላሚ የነበረ ነው፡፡ ይህ ብሄራዊ ጀግና ”ኡባተሌ” በተባለች የኦጋዴን ቀበሌ ውስጥ ጦራችን ከእብሪተኛው የሶማሊያ ወራሪ ጦር ጋር ወሳኝ ፍልሚያ በሚያደርግበት ጊዜ በፈጸመው ልዩ የጀግንነት ተግባር ሳቢያ ሊሸለም የቻለ ነው፡፡ ጀግናው የመቶ አለቃ በቀለ በላይ፣ በወገን ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ ወደ ፊት በመገስገስ ላይ በነበረ የጠላት ታንክ ላይ ወጥቶ የእጅ ቦምብ በመወርወር፣ ታንኩንና በውስጡ የነበሩትን የሶማሊያ ጦር አዛዦች ዶግ አመድ ያደረገ አንበሳ ነው፡፡ ለሸጋው ብእርተኛ ለሰለሞን ለማ ገመቹ ተርኮለት ላይነ ንባብ የበቃው ይህ መጽሃፉ እጅግ አስደናቂ የጦር ግንባር ውሎዎችን ገድል እስክ ኢሕአዴግ እስር ቤቶች ጓዳ ድረስ የሚያስቃኝ መሳጭ ሥራ ነው፡፡

Abera Lema, Author4

የመቶ አለቃ በቀለ በላይ ሁለት ዓመት ተመንፈቅ ያህል በእስር ቤት ከተንገላታ በኋላ፣ በሥራ አጥነት ያሳለፋቸውን መራራ ዓመታት ሰቆቃውን በዝርዝር አሳይቶበታል፡፡ እንደሱ ሁሉ ጀግኖች የነበሩትን የትግል ጓደኞቹን የነአሊ በርኬንና የመሳሰሉትን የድህረ ኢሕአዴግ አስከፊ መጨረሻቸውን ሁሉ ያስቃኘናል፡፡ እስር ቤት ውስጥ እያለ ከኢሕአዴግ ካድሬዎች ጋር ጉሮሮ ለጉሮሮ ተናንቆ፣ ለቆመለት ዓላማና ለታገለለት እውነት ዛሬም ጸንቶ እንደሚቆም ማረጋገጡን፤ አድምቆ ጽፏል፡፡ ከተከራከረባቸው ብርቱ ነጠቦች አንዱ የኢሕአዲጉ ካድሬ፣ የሶማሊያ ወረራ ሕጋዊ ያፍሪካ ልጅ ግብር ነውና እሱን ገድለህ ጀግና የተባልክበትን አሳፋሪ ሥራህን ይቅርታ ልትጠይቅበት የሚገባ ነው ይለዋል፡፡ መቶ አለቃ በቀለ ግን ባቋሙ ጸንቶ፤ ለካድሬው የማይታሽ፣ የማይቆረጠም የብረት ቆሎ ይሆንበታል፡፡ ለዚህ አቋሙ የተቀበለው ምንዳ ቢኖር እስከ ጨለማ ቤት ድረስ መታሰር ነበር፡፡ የእስር ክፍሉም ”ዘረባ ግደፍ” እንደሚባል በመጽሐፉ ላይ አመላክቷል፡፡ (ከገጽ 255- 260 ይስተዋላል)

Abera Lema, Author5ይህ መጽሀፍ የተረሱትን ያገራችንን ጀገኖች እንድናስታውስና፤ ተተኪውም ትውልድ በጀግንነት ሙያቸው አርአያ የሚያደርጋቸው አባቶችና እናቶች እንደነበሩት የሚያሳይ ምልክት እንዲቀረው የሚጠይቅ ነው፡፡ የትናንት ያገር ባለውለታዎችን ዛሬ ማስታወስና መንከባከብ ካልቻልን፣ የነገው የኛ እጣ ፈንታ ደሞ የባሰ ይሆናል የሚል ስጋቱን ባለታሪኩ አስምሮበታል፡፡

በነገራችን ላይ ይህ የጀግናውን የመቶ አለቃ በቀለ በላይን ገድል የሚያወሳውና በሰለሞን ለማ ገመቹ የተጻፈው መጽሐፍ በሲዲም ተቀርጾ ቀርቧል፡፡ ድምጸ ሸጋው ሻምበል አክሊሉ ዘለቀ አሳምሮ ተርኮታል፡፡

የመቶ አለቃ በቀለ በላይ ታሪኩን የቋጨበትን የመጨረሻ ምእራፍ የከፈተበትን ይህን አንድ አንጓ ግጥም ላንዳፍታ እናጣጥምለት፡፡

”የትላንቱ ነገር ይኽው ሆነ ዛሬ
እድሜ ለትዝታ ድሮን አየሁ ኑሬ”

እኒህ በቅርቡ የወጡ የጦሩን ሕይወትና ታሪክ የሚያዘክሩ ሁለት መጽሐፍት፣ ያተራረክ ስልታቸው ቀላልና ለማንኛውም አንባቢ ዐይነ ግቡ የሆኑ ናቸው፡፡ በቋንቋ አጠቃቀም ረገድ መደበኛውን የብዙሃን የዘወትር ዘዬና አንጋር ተጠቅመውበታል፡፡ በየምእራፉ መሪ ርእስ እየሰጡ የተለያዩ ጉዳዮችን በማነሳታቸው፣ ያንባቢን ስሜት ተቆጣጥሮ ለማቆየት የሚያስችል ያጻጻፍ ዘዴን ተከትለዋል፡፡ የጽሁፍ ለዛንም ተውበውበታል፡፡ በመረጃ አቅርቦት ረገድም ብርቱ ጥንቃቄ ማድረጋቸውን ከሥራቸው ማስተዋል ይቻላል፡፡ በዋቤ መጻሕፍትና በግርጌ ማስታወሻዎች ታግዘዋል፡፡

”ትውልድ ያጫረሰ ጦርነት” የሚለውን የሻለቃ ንጋቱ ቦጋለን መጽሃፍ (nigebogo@yahoo.com) ከሰሜን አሜሪካ የኢትዮጵያውያን መደብሮችና ከአገር ቤት ማግኘት ሲችሉ፤ ”የጀግና ወሮታ” የተባለውን ሰለሞን ለማ ገመቹ ያጠናቀረውን መጽሐፍ ደሞ ካዲስ አበባ (ስልክ ቁ. 0911791931) ማግኘት እንደሚችሉ ኣሳስባለሁ፡፡

Posted by Hellen Tesaye

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s