ልክየለሽ ራስ-ወዳድነት ሰላምና ነፃነትን የሩቅ ህልም እንዳያደርግብን

ዳኛቸው ቢያድግልኝ

‘ኢጎ’ (Ego) ቃሉ ከግሪክ የተወሰደና ትርጉሙም ‘እኔ’ ወይም ‘እኔነት’ ማለት ነው። ‘እኔ’ና ‘እኔነት’ ራስን ማወቅ፣ መሻትና አሻራ መተውን ደምሮ ህልውናን የሚገልጽ የንቃተ ህሊና አካል ነው። ይህ ስሜት መጠኑን ሲያልፍና ሌላውን አሳንሶ ራስን መሪ፣ አለቃ፣ ቀዳሚ፣ አዛዥ አድርጎ መቁጠር ሲጀመር ወደ (egoist, narcissist) ግለኝነት እኔ ብቻ ወደ ማለት ያድጋል። ነገር ግን ‘ኢጎ’ን በጥቅሉ  መጥፎ ቅንፍ ውስጥ መጨመርም ስህተት ይሆናል። ምክንያቱም አኔነትን ማለትም እራስን ማወቅ መሰረታዊና አስፈላጊ ጉዳይ ነውና። ይህ ጽሁፍ የሚያተኩረው ልክ-የለሽ እኔነት ወይም ራስ-ወዳድነት  (egoism) ላይ ነው። በርካቶችን “ከእኔ በላይ ለአሳር” በሚያሰኝና እንኳን የሚመኙትን ስልጣን ማጣት የሚኖሩበት አገር መፍርስም ቢሆን እንኳ ከመቻቻል ይልቅ ተያይዞ ገደልን የሚያስመርጥ ውስጣዊ ስሜት ያንጸባርቃሉ። ይህም ጽሁፍ በዚህ ላይ ያተኮረና መፍትሄም አመላካች ይዘት ያለው መልዕክት የማቅረብ መኩራ ያደርጋል። ኢጎ ከልክ ያለፈ ሲሆን ግን ሰው እራስ ወዳድ የሆነና በአህያ እንደተረተው እኔ ካለሁ ሁሉም ለኔ ይኑር አዝማሚያ ያለው  “እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል” አለች እንደሚሉት አይነት ባህሪይን ያላብሳል። ሥዕሉ ይህንን ሀሳብ በመጠኑ ይገልጸዋል የሚል እምነት አለኝ።The self, especially as distinct from the world and other selves

ኢጎ ለራሳችን ስለራሳችን በምናባችን አጋነን የምንፈጥረው ምስላችን ነው ይሉናል ጠበብቶች። መገለጫውም ራሳችንን የምናሞካሽበት ምስል፣ የምንሸሸግበት ጭንብል እና ሌሎችን ከኛ አሳንሰን የምንፈርጅበት መንገድ ሲሆን እውነተኛ ማንነታችንን ገላጭ ያልሆነ አለቅጥ እንድንኮፈስ የሚያደርገን ውስጣዊ ስሜት ነው። የኢጎና የንቃተህሊና ዝርዝር እውቀቱ በሁለት ገጽ የሚካተትም አይደለም። በዚህ ላይ ባለሙያዎች ጥሩ ሊያስተምሩበት ይችላሉ። ጸሀፊው ግን የባህርይ ሳይንስን በተመለከተ የጠለቀ እውቀት እንደሌለው አንባቢውን ከወዲሁ ያሳስባል።

ከዘመነ መሳፍንቱ ከፍና ዝቅ፣ ከተማሪ ረብሻና ከዘመነ ደርጉ ሽኩቻ አሁን እስካለንበት የተቃዋሚዎች ልፊያና ጥድፊያ ድረስ የስህተት ጎዳና ውስጥ የሚከተን በአብላጫው ያበጠ ኢጎ እንጅ የዓላማ ልዩነት፣ ጉልበት እንጂ እውቀት እንዳልሆኑ መመስከር አጥንት ድረስ ዘልቆ ያማል። ይህ ስውሩ የእኔነት ፈታኛችን በተሰባሰብንበት አጥቢያ፣ በምንጸልይበት ቤተክርስትያንና መስጊድ ሁሉ አብሮን ይኖራል። ይኸው ጥላችን በምንሰራባቸው መስሪያ ቤቶች፣ ፈቅደን በምናቋቁማቸው ሕዝባዊ ድርጅቶቻችን፣ በምንዝናናባቸው ስፍራዎች ሳይቀር አብሮን አለ።  ቤተሰብና ጓደኞች መካከልም ተደላድሎ ኗሪ ነው። እኛ ያለንበት ‘እኔነት’ም ይኖራል።

የተጋነነ እኔነት ሌሎችን ስለሚያሳንስ የቅራኔ፣ የመናናቅና የጥላቻ ምንጭ ይሆናል። የተሸነፈ እኔነት (ኢጎ) ቂመኛነትንም ሊወልድ ሲችል የተመቸው ደግሞ አምባገነን፣ አግላይና ጽንፈኛ እስከመሆንም ይደርሳል። ኢጎ እየጨመረ በመጣ መጠን በአንድም ይሁን በሌላ መልኩ ግለሰብ ከማህበረሰብ እየተነጠለ ይሄዳል። ምክንያቱም ትኩረቱ በራሱ ለራሱ ብቻ እየሆነ ስለሚመጣና እኔ የሚለው ሰብዕናው አድራጊና ፈጣሪ እርሱ ብቻ እንደሆነ ስለሚነግረው ማለት ነው።

ኢጎአችን ሲያንቀጀቅጀን “ማን እንደኔ!” እንድንል እያደረገ ሲቻል በጉልበት ሳይሆን በመሰሪነት ሌሎችን ለመጥለፍ እንደ አንዳች ሲያጣድፈን፣ ልጓም የሚሆነን ሰፊው ህሊናችን (Consciousness) ነው። ህሊናችን ኢጎን ጨምሮ የምናውቀውንም (ንቃተ ህሊና) ሆነ እውቅና ያልሰጠነውን ያለና የሚኖር ነገርን ጨምሮ የሚይዝ በመሆኑ ከእኔነት በላይ ሌሎች ነገሮችም እንዳሉ ሌሎች ሰዎችም እንዳሉ ያሳውቀናልና ነው። በዚህ አንፃራዊ ሚዛንም እኔን ከሌላው ጋር እያስተያየን  እንድንመለከት ይረዳናል። ሕሊናችን አቅማችንን እንድንለካና አካባቢያችንን ወይም ዐለምን ቃኝተን ወደ ቦታችን እንድንመለስ ያደርገናል። ሀይማኖት ጠበቅ አድርገን ለምንይዝ “አረ ፈጣሪም ያየኛል” የሚያስብለን ሕሊና ነው። አንዳንዴም ደንገጥ ብለን ራሳችንን እየወቀስን “ እንዴ ምን ነካኝ?” እንድንል ያደርገናል። ጭለማ በብርሀን እንዲገፈፍ ሁሉ ኢጎም  በንቃተ ሕሊና ይገራል።

ምናልባትም ያበጠ ኢጎና (ማለትም ለራስ የተጋነነ አመለካከት መያዝና) ንቃተ ህሊና፣ አለቅጥም እንዳንልፈሰፈስ አላግባብም እንዳንኮፈስ የሚያደርጉ ውስጣዊ ስሜቶች ናቸው ብንል ቀለል ያለ የማገናዘብያ መንገድ ይመስለኛል። ኢጎ ከሌላው የሚነጥለን እኔነት ሲሆን ህሊና ከሌላው የሚያግባባን አብሮነት ማለት ነው። ፈረስን እንደሚያሰግሩት አንበሳንም እንደሚያለምዱት ሁሉ ኢጎን መግራት መቻሉ የአብሮነት የማህበራዊ እንስሳነት ግዳጃችን ነው። ማህበራዊ እንስሳት  የመኖራቸውን ዋስትና የሚያገኙት ወይ ጡንቻ ላለው ንቁና ጎበዙ፣ ወይም የዘመን ብዛት የኑሮ ዘዴን ላስተማረው አዛውንት፣ ወይም ለልጆችዋ ለመሞት ወደ ሁዋላ ለማትለው የእናቶች ቁንጮ በመታዘዝ ነው። ከመንጋው ከተለዩ የአንበሳው፣ የጅቡ የተኩላው የነብሩ እራት ስለሚሆኑ ትውልዳቸው ቀጣይነት ላይኖረው ጭራሹኑ ሊጠፉም ይችላሉ።  ይህ በደመነብሳቸው የሚረዱትና  ከዘር መጥፋት የሚድኑበት አንደኛው መንገዳቸው ነው። አዳኞቹ አንበሶች፣ ዘንጣዮቹ ጅቦች፣ ተናካሾቹ ተኩላዎች ሳይቀሩ የአብሮነትን ዋጋ አሳምረው ያውቁታል። ለራስ ወዳድነት ምልክት የምናደርጋቸው ጅቦች እንኳ፣ ተጋግዘው ይገድላሉ፣ ተጠራርተውም ይበላሉ። እናም ተረዳድቶ መኖር የህልውናቸው ዋስትና እንደሆነ ትምህርት ቤት ሳይሄዱ ኮንፈረንስ ሳይጠሩ ያውቁታል። ተጋግዘውና ተከባብረው፣ ቅራኔያቸውን አቻችለውና አንድነታቸውን አስከብረው የማይኖሩቱ ሰዎችም በህልውናቸው ላይ ፈርደዋልና ጠንካራ አጥፊም አያስፈልጋቸውም።

የሰው ልጆች በተለይም እኛ ኢትዮጵያውያን አገር ጠልተው ብሄረሰብን፣ ብሄረሰብ ንቀው መንደርን፣ መንደርን ረግጠው ቤተሰብን፣ ቤተሰብን አጣጥለው ራስን ብቻ የሚያደንቁ አጨራረሳቸው ጥፋት ብቻ የሆኑትን  ‘ስማርት’ እያልን  ስናደንቅ የፖለቲካ ተንታኝ እያልን ከፍ ከፍ ስናደርግ የኛው ኢጎ እኛው ላይ እያበጠብን እንደሆን አናስተውልም።  ለቃል እንጂ ለትርጉሙ ሳንጨነቅ አንዱ ያለውን እየደገምን የጥፋቱን እሳት እያራገብንም እንኖራለን። ለዚህ ነው ነገሮችን ሁሉ ለአለሁ አለሁ ባዮችና አዋቂ ነኝ ባዮች  መተው ትክክል የማይሆነው።

የመነጋገር ባህል፣ የመተራረሚያ ቋንቋ፣ እውነት የመናገር አቅምና ገንቢ የሆነ ሂስ ያበጠን የግለሰብ ኢጎ ወደተስተካከለ እውነታ የመመለስ ሃይል አለው ይህንን ግለሰቦችም ይሁኑ ማህበረሰቡ ሊቀበልና ያለውንም ሊያዳብር ይገባዋል። ይህንን የመረጥን እንደሁ አጥፊውን መተቸትና ድጋፍ መንፈግ ጥሩውን ደግሞ ማመስገንና መደገፍ ልክ ሰላም ለማለት እጅ የመዘርጋትንና አዎ ለማለት አንገት የመነቅነቅን ያህል ቀላል የሆነ ትክክለኛውን ብቻ የመደገፍ  ልማድ ይኖረናል። ይህም እያደገ ከመጣ ለመጥፎ ባህሪይ ብከላ አመቺ ሁኔታ አይኖርም፣ የክፋት ተስቦም አይራባም።

‘ኢጎን’ ወይም እኔነትን አስመልክቶ እኔም የሚሰማኝን እንጂ ጠልቄ የማውቀውን እየጻፍኩ አይደለም። በመጀመርያ በሙያው የሰለጠንኩ በጉዳዩ ላይም የተጠበብኩ ወይም የተመራመርኩ አይደለሁም ብዬ ራሴን በይፋ ገልጫለሁ። ስለሰው ልጆች ባህሪይ የማውቀው ትንሽ በመሆኑ ጽሁፌን የሚያነቡና እናውቃለን የሚሉ ኢጎይስቶች ከትከት ብለው ሊስቁና ሙልጭ አድርገው እየሰደቡ አላዋቂነቴን ሊናገሩ ሲችሉ ለህሊና ያደሩ ደግሞ  ሙከራዬን ይሁን ብለው የሚያውቁትን ለማሳወቅ ስህተቴንም ነቅሰው ሊያርሙ ይችላሉ።  በቀላሉ ከኔ የበለጠ አዋቂ የለም ብሎ ያለመኮፈስና አላዋቂ ብሎ ከሚሳደበው እንዲህ ይመስለኛል ብሎ የድርሻውን የሚያበረክተውን የመቀበል ምርጫ ነው ወደ ራስን ማወቅና አልፎም አካባቢን መረዳትም  የሚያመጣን። አንዳንድ ልቅ አምባገነኖች ሌሎችን በማኮሰስና በማንጓጠጥ ሲዘልፉ አላዋቂነታቸውን ለእይታ ሲያቀርቡ በሳቅ እያጀብናቸው ሁዋላ ሁላችንም መሳቂያ መሆናችንን ልብ ይሏል።

በጣም የተማሩ ባለ ብዙ ዲግሪዎችን ጨምሮ ዱላ ቀረሽ ስድብን ሲያወርዱ ራሳቸውን ሽቅብ ቆልለው ሌላውን ቀለም ያልገባው፣ እውቀት የራበው አድርገው እንደ እውቀት የሚያካፍል አስተማሪ ሳይሆን እንደ ጉልበተኛ አከርካሪ ለመስበር ስብዕና ላይ ጭምር ሲዘምቱ መመልከት የተለመደ ነው። እንዲህ አይነት ኢጎ ሲኖር ውይይት ወደ ስድብና ዘለፋ ያሸጋግራል። ለዚህ ነው የውይይትና የመደማመጥ አቅም እያነሰን ወደ መገዳደል ለመዞር ያልቦዘንነው። ለአንድ ሀገር ሕዝብ ለተመሳሳይ ዓላማ ተበታትኖ መደራጀትንና የኔ ይበልጣል ማለት የመረጥነውም በዚሁ ምክንያት ነው። ተመሳሳይ ዓላማና ግብ ይዣለሁ ብሎ የተበታተነ ድርጅት የሚገነባውና የሚያፈርሰው ሁሉ ልብ የማይለው ነገር ቢኖር ራሱን ከመሰሎቹ ማወዳደር ላይ እያተኮረ ዋንኛ ተቀናቃኜ አልፎም ጠላቴ የሚለውን እንዲረሳና ከተነሳበት ዓላማውም እንዲዘናጋ ማድረጉን ነው። አንድን ድርጅት ለማገዝ ተሰባስበን በውስጣችን ባለው ኢጎ ምክንያት እንደግፍ የምንለውን ድርጅት የሚጎዳ ነገር ስናድረግ እንኳን ልብ የማንል፣ ልብ ካልንና ካወቅንም ደንታ የማይሰጠን  ብዙ ነን።

በርካቶች እንደምንስማማበት እንደ ሀገር እየቀጨጭን እንደ ሕዝብም ቁልቁል እየሄድን ነው። እነዚያ ያልተማሩ የምንላቸው አያት ቅድመ አያቶቻችን፣ የዓለም ሀያላን ሀገሮች በመሰሪ ተንኮላቸው የመርዝ ጭስ እያርከፈከፉባቸው የቦንብ ዝናብ እያወረዱባቸውም ሀገርን ለትውልድ ለማቆየት ሲባል ያንን ሁሉ መስዋዕትነት ከፍለው በርካቶች የሚኮሩባት፣ አርአያም የሆነች ሀገር አስረክበውን አልፈዋል። እነርሱ በመስዋዕትነታቸው ከአንገታችን ቀና እንድንል እንዳላደረጉን ዛሬ ‘ኢትዮጵያዊነት በጉልበት ተጫነብኝ’ የሚሉ እንጭጭ ህሊና ቢሶችና ሀፍረተ ቢሶች ሳይወክላቸው ቆመንልሀል የሚሉትን ኩሩ ሕዝብ ገድልና አስተዋጽኦ ሲያኮስሱ እናያለን። እነኚህን  የጥላቻ ወኪሎች እንዲሆኑ የሚገፋፋቸው ትንንሽ መንግስታት ተፈጥረው  ‘መሪ’ የመሆነን ፍላጎታቸውን  ኢጎ ነው።

ለዚህች ኢትዮጵያ ሕልውና አስተዋጽኦ ያደረጉ ሁሉ ተከብረው የሚኖሩባትን ታላቅ ሀገር እንፍጠር ከሚል ሀሳብ ስንነሳ ግን ትምክህትና ጥላቻ በንቃተ ህሊና ይተኩና በአፍራሽነት ምትክ ምክንያታዊነት ይጎለብታል። እንደ ሕዝብ ያንን ማድረግ ካልቻልን የኛን ትምክህት ለሚያንጸባርቁልን እየሰገድን ቁልቁል መሄዱን እንቀጥላለን። ወይም ፍርሀታችንን ሁሉን በምንንቀበት ማስክ ሸፍነን ዳር እንደቆምን ደራሽ የፖለቲካ ጎርፍ ጠራርጎ ወዳሻው ይወስደናል።

ባለፉት አመታት ተባበሩ በሚል ግፊያ ሳቢያ ብዙ የወል ስም ያላቸው ስብሰቦች ራሳቸውን ሲያስተዋውቁ ሰንብተው አሁን እጅግም አይታዩም። አሁን ደግሞ ጊዜው የሰላማዊ ሰልፍ ሆኖልናል። አቶ ሀይለማርያም እየፈረሙ ወይዘሮ አዜብ ሰላማዊ ሰልፍ ሰፖንሰር እያደረጉም ድርጅቶችን ሁሉ ቢያሰልፉ ሰላማዊ ሰልፍ እንደወረት ዘፈን የአንድ ሰሞን ሆይ ሆይ ሆኖ ሊያበቃ የሚችል ነው ብሎ መስጋት ሞኝነት አይደለም። መፈክሮቹ በሙሉ አንድ አይነት ከሆኑ እንደ ጽዋ ሰልፉን በተራ ማዳረሱ ያሳሳል ኢንጂ አያጎለብትም። ደጋፊዎችን ያዳክማል ይከፋፍላል እንጂ ጉልበት አይሆንም። ስለዚህ የልዩነቱ መሰረት ‘ኢጎ’ ወይም ትምክህት በበታተናቸውና እኛም አይዞአችሁ በምንላቸው ወገኖች ምክንያት መሆኑኢ እውነት ነው። ይህ እውነት ከሆነ ደግሞ የሰልፍ መሪዎች ትኩረት የሚሆነው በሚገኘው ውጤት መሆኑ ይቀርና ማን ምን ያህል ሰው አሰለፈ? ምን ያህልስ ገናና ሆንኩ? የሚለው የእርስበርሰ ውድድር ይሆናል ። ይህ የቁጥር ሽሚያ ደግሞ ሰርገው ለመግባት ለሚሹት አፍራሾች መንገድ ከፋችም ነው። ይህንን ማድረግ ደግሞ ለገዢዎቹ ምቹ ነው። አንዱን ሲያስሩ ሌላው ፍቱልን እንዳይል በድርጅት ተከፋፍሏልና ተነጣጥሎ ይመታል። ከመንጋው የተለየ እንስሳ የአዳኞች ሥራን እንደሚያቀልላቸው ማለት ነው። የእስልምና ተከታዮችም እንዲሁ ትግሉን ከእምነት ነፃነት በላይ የኢትዮጵያውያን የነጻነትና የህልውና ጥያቄ አድርገው ሁሉን አቀፍ ትግሉን ካላጠናከሩት ዳር ቆሞ ተመልካችን ወደመሀል ማስገባተ ሳይችሉ ተራ በተራ ሊመቱ ይችላሉ። ያለብን ችግር እንደ ሀገር የመኖር እንጂ የ እምነት ነፃነት ማጣት ብቻ አይደለምና።

ወደ ሕዝቡ ስንመለስ ደግሞ የሀገራችን ሕዝብ ለውጥ ይፈልጋል። መሪ የሚሆነወንም በመፈለግ ላይ ነው። በዚህ ዝግጁነቱ ሳቢያ እንመራለን የሚሉ ድርጅቶች በመጡ ቁጥር አባላት የማግኘት እድላቸው ሰፊ ነው። በሌላ ጎኑ ድርጅቶችን አጥንቶ መርምሮና ጠይቆ አባል ለመሆን ልምድ አለመዳበሩ ለነዚህ ድርጅቶች ማደግ ምክንያት ይሆናል። እገሌ የኔ ሰው ነው እሱ ያለበትን መደገፍ ግዴታዬ ነው በሚል ስሜት ብቻ ታማኛነታቸውን ለመግለጽ የማያምኑበት ድርጅት ውስጥ የሚገቡም አሉ። አብሮን ረዥም አመት የዘለቀው ችግር ደግሞ የፖለቲካ ድርጅት ውሰጥ በመቆየት፣ ክፉና ደግ በማሳለፍ፣ ማህበራዊ ህይወትና ዝምድና በማጠናከር ብቻ ከፖለቲካው ድርጅት ይልቅ የቡድንና ‘እኛ ብቻ ጀግኖች’፣ ‘እኛ ብቻ የፖለቲካ አዋቂዎች’ የሚል ድርጅታዊ ኢጎ ፈጥረው በሚያምኑበትና በመረዳታቸው መጠን ሳይሆን ድርጅት አምላኪ በመሆን ለራሳቸው በምናባቸው የጀግና ሀውልት ሰርተው የሚንቀሳቀሱቱ አሉ። የሚገርመው አደረጃጀታቸውና ስነምግባራቸው እንኳን ዘመን መሻገር ያልቻለና በስም ማጥፋት ዘለፋና ልክ እንደ ወያኔ ተለጣፊ ድርጅት በማቋቋም ሌላውን የሚታገሉ ወይም የሚያዳክሙ አሉ። እንደዚህ ያለ ስብስብ ውስጥ በድርጊቱ የማመን ሳይሆን በአብሮነቱ ለመቆየትና ላለመገለል ሲሉ ብቻም የቡድን አባል ሆነው ከሁሉም በፊት ድርጅት ብለው ጽዋ የሚያነሱ አሉ። ይህ ሁሉ ተዳምሮ ከነበርንበት ወደ ተሻለው እንዳንሄድ ያደርገናል። የዚህ ሁሉ ምንጩ ደግሞ ቆመንለታል የምንለው የፖለቲካ ዓላማ ሳይሆን አቁሞ ያኖረናል ብለን የምናምንበት ኢጎ መሆኑ ነው።ኢጎይስትነት መለያ ባህሪው ሁልጊዜም ራስን አገዝፎ መመልከት ስለሆነ ካለፈው መማርም ሆነ አሁን ያለውን ነባራዊ ሁኔታ መገንዘብና መመርመር አያስችልም። ይህ ደግሞ ስለወደፊቱም ለመተንበይ አቅም ያሳጣና  ከስህተት ወደ ባሰው ጥፋት ይወስዳል።

ስለዚህ በእኔ እምነት ኢትዮጵያችን አሁን ያለችበት ሁኔታ አደገኛና አሳሳቢ ነው ብለን የምናምን ሁሉ በማድረግም ሆነ ባለማድረግ፣ በመሳተፍም ሆነ ዳር ቆሞ በመመልከት የዛሬው ሁኔታ እንዲፈጠር በማድረጌ እንደትውልድ ጥፋተኛ፣ እንደ ትውልዱ አባል ተጠያቂ ነኝ ከሚል የጋራ ሀላፊነት በመነሳትና እነ እገሌ የሚለውን በመተው ከራሳችን መጀመሩ የመግባቢያ አሀዱ ይሆናል። ሁላችንም ጥፋተኞች ነን ብለን ካመንን ለጊዜው ከሳሽ አይኖርም። ካላመንን ግን በሌሉበት ሀገር ያቆዩንን አያት ቅድመ አያቶች የምናደንቀውን ያህል መጪው ትውልድ በሌለንበት ይፈርድብናል ማለት ነው። ይህ እንዳይሆን ተቀራርቦ መነጋገር፣ ይቅር ብሎ መተቃቀፍና አንድ ላይ እንስራ ብሎ መደጋገፍ የግድ አስፈላጊ ነውና  ከኔ ይጀመር በሚል ዛሬውኑ  መነሳሳት ይገባናል።

ወደ ማጠቃለያችን ለመድረስ እንዲህ ብለን ራሳችንንም ሌሎችንም እንጠይቅ ለመሆኑ ዓላማችን ስልጣን ለመያዝ ነው? ወይስ ስልጣን የምንፈልገው ዓላማችንን ለማስፈጸም ነው? ጥያቄውን በሚገባ መመለስ የግለሰብንም ሆነ የድርጅትን ፍላጎት የማሳየት አቅም አለው። ዓላማችን ስልጣን መያዝ ከሆነ ስልጣን እጃችን ሲገባ ግባችን ላይ ደርሰናል። ስለዚህ ከዚያ በሁዋላ የሚሆነው እንደ ባለስልጣኑ ፍላጎት ይሆናል። ስልጣን ዓላማን ለማስፈጸም ሲሆን ግባችንን አንድ ብለን መቁጠር የምንጀምረው ዓላማዎች መተግበር ሲጀምሩ ይሆናል። በዲሞክራሲ ስም ተነስተው የለየላቸው አምባገነኖች የሚሆኑበት ምክንያትም በአብዛኛው ስልጣን ግብ ሲሆን ነው፡፡

ከዚህ ከተነሳንና ምርጫችን ወደ ሁለተኛው ከሆነ እብሪታችን ጠፍቶ ትምክህታችን ተንፍሶ ንቃተ ህሊናችን ጎልብቶ መድረኩን ሲረከብ ወደ ብሄራዊ እርቅ የሚወስድ ሁሉን አቀፍ ንግግር መጀመር ይቻለናል። ያኔ አዲስ ነገር ተቋቋመ በተባለ ቁጥር አደራጅና መሪ ሆነው ቀድመው የሚታዩትና የጀመሩትን ጥለው ወደ ሌላ አዲስ ጅምር እሽቅድምድም የሚሄዱትን ሁሉ ረጋ እንዲሉ ማድረግም ይቻላል። ሰዎች አስበውና አስተውለው የጀመሩትን ሞጭልፈው መድረክ ላይ የሚሾሩና ዳር ማድረስ የማይችሉ ‘ሁሉ አማረሽ’ የሆኑትንም መምከር ይቻላል። በአዲስ መንፈስና ስሜት የአቅማችንን፣ የችሎታችንን፣ የድርሻችንን በመስጠት ልንሰራ ያሰብነው እንኳን በሌሎች ከተሰራልን፣ ሞክረን ያልቻልነው በሚችሉና ጊዜው የሚጠይቀውን በሚረዱቱ ከተሰራ በደስታ ልናርፍ ወይም ሌላ ነገር ልንሰራ እንችላለን። የምንመለከተው የስራውን ውጤት እንጂ እገሌ ሰራው ተብሎ መወደስን ካልሆነ ተባብሮና ተደጋግፎ መሄድ ቀላል ይሆናል። ያ ደግሞ የሚሰጠው ደስታ በቃላት የሚመጠን በገንዘብ የሚተመን አይደለም። መስራት ከፈለግን የሚሰራ ነገር አንሶ አያውቅም፣ የሰሩትን ስናመሰግን የሰራነውም መታወቁ እርግጥ ነው።

ኢጎ በነገሰባት ኢትዮጵያ ሰላምና ነፃነት የሩቅ ህልም እንዳይሆኑብን ጭምብላችንን ወይም ማስካችንን ገልጠን፣ “እኔ! እኔ ብቻ!” የሚለው ስሜታችን ሰክኖ፣ እውነተኛ ማንነታችንን (ችሎታችንና ድክመታችንን) አውቀን የሄድንበትን ጎዳና መለስ ብለን ለመመልከት እንቻል። ከዚያም ዛሬ የደረስንበትን በማጤን የነገ ሕልማችንን  በንጹህ ህሊና ተመልክተን በዚህች አንድ ጊዜ ብቻ በምንኖርባት ዐለም የእውነት እኛነትን ኖረን ለማለፍ ትክክለኛውን መንገድ እንምረጥ።  ምናልባት በሕይወታችን ፍጻሜ ላይ ራሳችንን የምንጠይቀው የመጨረሻው ጥያቄም ይኸው ሊሆን ይችላል። ያኔ የሕይወት ጀንበር መጥለቂያ በመሆኑ ፀፀት አይመልሰውም፣ ቁጭት አያክመውም። ያለፈ ቀን ታሪክ እንደመሆኑ ካለፍን የታሪክ አካል ብቻ መሆናችንም አውነት ነውና እያለን አንወቅበት።

http://ecadforum.com

Posted by Hellen Tesfaye

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s