የሸራተን ሠራተኞች የመብት ረገጣ እየተፈጸመብን ነው አሉ

 

-በደላቸውን ለጠቅላይ ሚኒስትሩና ለሁሉም የመንግሥት አካላት ገልጸዋል

‹‹በማላውቀው ነገር ላይ ምንም የምሰጠው ምላሽ የለም››

የሸራተን አዲስ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሚስተር ዦን ፒየር ሚኒጐፍ

በሸራተን አዲስ ከ15 ዓመታት በላይ በተለያዩ የሥራ ክፍሎች በመሥራት ላይ የሚገኙ ከ500 በላይ ሠራተኞች በሆቴሉ ሥራ አስኪያጅ፣ ዘርና ቀለምን መሠረት ያደረገ በደልና የመብት ረገጣ እየደረሰባቸው መሆኑን ለሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት አስታወቁ፡፡

  

የደረሳቸው ደብዳቤም ሆነ ሌላ ነገር እንደሌለና የሚሰጡት ምላሽ አለመኖሩን የሸራተን አዲስ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሚስተር ዦን ፒየር ማኒጐፍ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ 

ሠራተኞቹ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ለሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ለኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን፣ ለእንባ ጠባቂ፣ ለኢሠማኮና ለሌሎችም ለሚመለከታቸው አካላት ግልባጭ በማድረግ በዋናነት ለውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በጻፉት ‹‹መፍትሔ ያጣ ጥቃትና ችግር›› የሚል ደብዳቤ እንደገለጹት፣ ፈረንሳዊው የሆቴሉ ሥራ አስኪያጅ ሚስተር ዦን ፒየር ማኒጐፍ 15 ዓመታት አልፏቸዋል፡፡ በቆዩባቸው ዓመታት በሠራተኞች ላይ በደልና የሰብዓዊ መብት ረገጣ አድርሰዋል ብለዋል፡፡ የሚደርስባቸውን በደል ለሆቴሉ ሠራተኛ ማኅበር ጨምሮ ለሚመለከታቸው አካላት ሳይቀር አቤቱታ ቢያቀርቡም፣ ከሚደርስባቸው በደልና የሰብዓዊ መብት ረገጣ ሊያላቅቃቸው የቻለ አካል ባለመኖሩ ለመንግሥት አካላት ለማሳወቅ መገደዳቸውን አብራርተዋል፡፡ 

አብዛኛውን ጊዜ የአሠሪና ሠራተኛ ችግር ሲከሰት የተለመደ፣ በየዕለቱ የሚታይና የሚሰማ ነገር ቢሆንም፣ የእነሱ ግን በተቃራኒው ከአሠሪያቸው ማለትም ከባለቤቱ ጋር በስምምነት የሚኖሩ መሆኑን የገለጹት ሠራተኞቹ፣ ዋና ሥራ አስኪያጁ የተሰጣቸውን ኃላፊነትና ሥልጣንን መከታ በማድረግ እየፈጸሙባቸው ያለው ቀለምንና ዘርን መሠረት ያደረገ በደልና የሰብዓዊ መብት ረገጣ፣ ከልክ በላይ መድረሱን በደብዳቤያቸው አስታውቀዋል፡፡ 

የዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች መከበር እንዳለበትና ማንኛውም ሰብዓዊ ፍጡር ከሚደርስበት አካላዊ ጉዳት የመጠበቅ መብቱ በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 10(2) እና አንቀጽ 16 መደንገጉን የገለጹት ሠራተኞቹ፣ በሸራተን አዲስ ሌግዤሪ ኮሌክሽን ሆቴል ውስጥ ለተሻለ ሥራና እንጀራ ፍለጋ በሠራተኝነት እያገለገሉ ያሉ ሠራተኞቹ ሰብዓዊ ፍጡር መሆናቸው ተዘንግቶ፣ የፈረንሳዊውን ዋና ሥራ አስኪያጅ አፀያፊ ስድቦችን ችለው ከመቆየታቸው አልፎ፣ ሕገ መንግሥታዊ መብታቸው እየተደፈጠጠ መሆኑን በደብዳቤያቸው ዘርዝረዋል፡፡ 

የሥራ አስኪያጁን አይዟችሁ ባይነት ያገኙ ሌሎች የሆቴሉ ተቀጣሪ የፈረንሳይ ዜጎችና የተለያዩ ሥራዎች ኃላፊዎች፣ በኢትዮጵያውያን ሠራተኞች ላይ ድብደባና የአካል ማጉደል ጉዳት እያደረሱባቸው መሆኑን የገለጹት ሠራተኞቹ፣ ለአብነት ያህል የሆቴሉ ኬክና ዳቦ ጋጋሪ ክፍል ሠራተኛ በክፍል አለቃዋ ጆሮዋን በጥፊ ተመትታ ለሕመም መዳረጓን ጠቁመዋል፡፡ 

ሠራተኞቹ በደብዳቤያቸው እንዳብራሩት፣ የዋና ሥራ አስኪያጁን ዛቻና ማስፈራሪያ በመፍራት፣ አብዛኞቹ ሠራተኞች ለሚመለከተው አካል ለማሳወቅ ይፈራሉ፡፡ ዋና ሥራ አስኪያጁ ለሠራተኞቹ በአገራቸው ከነጮች በታች የሆኑት አስተሳሰባቸው ዝቅተኛ ስለሆነ መሆኑን፣ አንዳንድ ዘመናዊ ነገሮችንና ሌሎች ለኑሮ የሚያስፈልጋቸውን ቁሳቁስ ያሟሉትም ሸራተን በመቀጠራቸው እንደሆነ በመንገር በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 18(1) ላይ የተደነገገውን ከጭካኔ፣ ከኢ-ሰብዓዊና ክብርን ዝቅ ከሚያደርግ ነገር የመጠበቅ መብታቸው ተጥሶ እንደሚገኝ ሠራተኞቹ በደብዳቤያቸው አብራርተዋል፡፡ 

ለሕገ መንግሥቱና ሕገ መንግሥታዊ መብቶቻቸው መከበር የጥንት አባቶቻቸውና የቅርብ ወንድሞቻቸው መስዋዓትነት ተረስቶ፣ በእነሱ ላይ እየደረሰ ያለው የሰብዓዊ መብት ጥሰትና በደል እንዳንገፈገፋቸው የገለጹት ሠራተኞቹ፣ አይዞህ የተባለ የውጭ ዜጋ ሼፍ ‹‹እናንተ ኢትዮጵያውያን የምትፆሙት በረሃብ ያሳለፋችሁትን ጊዜያት ለማስታወስ ነው፤›› በማለት ተጠብቆና ተከብሮ የኖረን ሃይማኖታቸውን ጭምር እስከመተቸት መድረሱን፣ እየደረሰባቸው ያለው በደል የት እንደደረሰ የሚያሳይና መንግሥት ችላ ሊለው የማይገባ መሆኑን በደብዳቤያቸው አስታውቀዋል፡፡ 

የሰው ልጅ ዘመናዊ አሠራርና አኗኗር እየተከተለ ባለበት በአሁኑ ዘመን፣ እነሱ ኋላቀር በሆነ አኳኋን በውጭ ዜጋ እየተሰደቡና እየተደበደቡ በመሆናቸው የመሥራት ሞራላቸው መውደቁን፣ በራስ የመተማመን አቅም ማጣታቸውን፣ ዝቅተኝነት እየተሰማቸውና በገዛ አገሩ በቅኝ ግዛት እየኖረ ያለ ዜጋ ያህል እየተሰማቸው መሆኑን ሠራተኞቹ ለውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የጻፉት ደብዳቤ ያስረዳል፡፡ 

የተለያዩ የመንግሥት ባለሥልጣናትን ስም በመጥራት ‹‹በማንኛውም ሰዓትና ቦታ የለበስከውን የደንብ ልብስ አስወልቀን በጥበቃ ኃይሎች እናስወጣሃለን፤ የተራበ ሰው በከተማው ስለሞላ ወዲያውኑ ተተኪ ይመጣል፤›› እያሉ በማስፈራራት፣ በሠራተኛው ላይ እያደረሱት ያለው ግፍ ከልክ ያለፈ መሆኑን ሠራተኞቹ አሳውቀዋል፡፡ ሴት ሠራተኞች በወሊድ ምክንያት ቆይተው ሲመለሱ፣ ‹‹የት ይሆን የምመደበው›› በማለት እንደሚጨነቁ የሚያብራራው ደብዳቤው፣ ምክንያታቸውም በእርግዝና ወቅት ስለሚወፍሩ ሲመለሱ በቦታቸው እንደማይመደቡ በሥራ አስኪያጁ አስቀድሞ ስለሚነገራቸው መሆኑን ያብራራል፡፡ 

በከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ የተገነባውና ከኢትዮጵያም አልፎ የአፍሪካ ኩራትና ክብር የሆነው ሸራተን አዲስ ዋና ገጽታ መሆናቸውን የሚገልጹት ሠራተኞቹ፣ በአንድ የውጭ ግለሰብ የሚደርስባቸው በደልና የመብት ገረጣ መጠኑ ከልክ ያለፈና የሆቴሉን እንግዶች ሳይቀር ያሳዘነ መሆኑን በደብዳቤው ጠቁመዋል፡፡ ሠራተኞቹ በደብዳቤያቸው አብራርተው እንደጻፉት ጉዳዩ የአሠሪና ሠራተኛን ግንኙነት ከሚመለከተው በላይ በመሆኑ የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት፣ ባለቤቱ ሼክ መሐመድ አሊ አል አሙዲንም እንዲገነዘቡላቸውና በጥቂት የውጭ አገር ዜጎችና ጥቂት ጥቅመኛ ኢትዮጵያውያን አማካይነት እየተፈጸመባቸው ያለውን የንቀትና የጭቆና አስተዳደር እንዲያላቅቋቸው ጠይቀዋል፡፡ 

ሠራተኞቹ ባቀረቡት የአቤቱታ ደብዳቤ፣ ዋና ሥራ አስኪያጁ ሚስተር ዦን ፒየር ማኒጐፍ ላደረሱባቸው በደል በሕግ የሚጠየቁባቸው ሁኔታዎች እንዲመቻቹላቸው ወይም ነፃ የሚወጡበትን መንገድ መንግሥት እንዲያመቻችላቸው የጠየቁት ሠራተኞቹ መንግሥት ችግርና በደላቸውን፣ እየደረሰባቸው ያለውን የሰብዓዊ መብት ረገጣ ተመልክቶ ዕርምጃ ካልወሰደ፣ ዋና ሥራ አስኪያጁ በሠራተኛውም ላይ ሆኑ በሆቴሉ ላይ የበቀል ዕርምጃ ሊወስዱ እንደሚችሉ ሥጋታቸውን አስታውቀዋል፡፡ እነሱም ከዚህ በኋላ በሥራ አስኪያጁ ለሚወስድባቸው ማንኛውም ዕርምጃ አፀፋዊ ምላሽ ለመስጠት ዝግጁ ሆነው እንደሚጠብቋቸው አስረድተዋል፡፡ 

የሸራተን አዲስ ዋና ሥራ አስኪያጅ በደል ፈጽመውብናል በሚል ሠራተኞቹ ለመንግሥት አቤት በማለታቸው ምክንያት ማብራሪያ እንዲሰጡ በጸሐፊያቸው በኩል ጥያቄ የቀረበላቸው ሚስተር ዦን ፒየር ማኒጐፍ፣ ‹‹ባልደረሰኝ ደብዳቤና በማላውቀው ጉዳይ ላይ ምንም የምሰጠው ምላሽ የለኝም፤›› በማለት ዝምታን መርጠዋል፡፡ በዋናነት ከሠራተኞቹ ደብዳቤ የተጻፈለት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ በ15 ቀናት ውስጥ ምላሽ እንዲሰጥበት ስለተሰጠው ደብዳቤና በደብዳቤው ላይ ያለው ነገር ካለ ማብራሪያ ለማግኘት በተደጋጋሚ ወደ ሚኒስትሩ ጽሕፈት ቤትና ሚኒስትሮች ካቢኔ ጽሕፈት ቤት ብንደውልም ምላሽ ለማግኘት ሳንችል ቀርተናል፡፡  

ethiopianreporter.com

Posted by Hellen Tesfasye

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s