ጋዜጠኛ እስክንድርና አቶ አንዱለአም ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ ቀሩ

ኢሳት ዜና:-ቃሊቲ ማረሚያ ቤት፤ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋንና አቶ አንዱአለም አራጌን ፍርድ ቤት ሳያቀርብ ቀርቷል። የፍርድ ቤቱ ፖሊስ ለእስር ቤቱ ሀላፊዎች ደብዳቤ ማድረሷን ገልጻለች።

የፌደራል ጠ/ፍርድ ቤት በ አቶ አንዱ አለም አራጌ የክስ መዝገብ በፌደራል ከፍተኛው ፍርድ ቤት በሽብርተኝነት ወንጀል የተፈረደባቸውን የ አንድነት ፓርቲ ም/ል ሊ/መንበር እና የህዝብ ግንኙነት ሀላፊ አቶ አንዱአለም አራጌ ፣ የአንድነት አመራር አባል ናትናኤል መኮንን፣  ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ፣  የቀድሞው የፓርላማ ተማራጭ አቶ አንዱአለም አያሌው ፣ የመኢዴፓ ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ሀላፊ አቶ ክንፈሚካኤል ደበበ ፣ አቶ ዮናስ ተረፈ፣ እና ሻምበል የሽዋስ ይሁን አለም የይግባኝ አቤቱታ በአግባቡ አለመመርመሩን ገልጿል።

የፌደራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤትን ውሳኔ ለማድመጥ የተከሳሽ ቤተሰቦች ፣ የአገር ውስጥና የውጭ አገር ጋዜጠኞች፣ የሰብአዊ መብቶች ተሟጋቾች እና የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች በርካታ ወጣቶች የተገኙ ቢሆንም ፣ ዳኛው አቃቢ ህጉንና የተከሳሽ ጠበቆችን ጠርተው በማነጋገር ጥቂት ጋዜጠኞች ብቻ ችሎቱን መታዘብ እንዲችሉ አድርገዋል።

በእለቱ ችሎት የተሰየሙት ዳኛ አቶ ዳኘ መላኩ ብቻ የነበሩ ሲሆን የእስረኞች ጠበቃ አቶ ደርበው ተመስገን ፣ አቶ አበበ ጉታ እና የመንግስት ጠበቃ አቶ ሳሙኤል አባተም ተገኝተዋል። ዳኛው ዳኘ መላኩም ለጠበቆች “እናንተ ምንም የምታምኑት ነገር የለም፣ አቃቢ ህግ ያለምንም የሰው  እና የሰነድ ማስረጃ  ክስ ስላቀረበ ብቻ ነው የተፈረደባቸው ፣ እኛ በ አግባቡ ተከላክለን እያለ ነው የተፈረደባቸው ስላላችሁ መዝገቡን በአግባቡ ሀ ብለን እየመረመርን ነው፣ በዚህም ላይ የፌደራል ፍርድ ቤት መዝገቡን አዘግይቶ ነው የላከልን ስለዚህ ለእናንተም በአግባቡ ቢመረመር ጥሩ ነው” በማለት ተናግረው፣ እስር ቤቱ እስረኞችን ለምን እንዳላቀረባቸው የእስር ቤቱን ፖሊስ አዛዥም እንጠይቃለን ብለዋል።

አንዲት ፖሊስ  ቀርባ  ” እኔ የማቅረቢያ የጥሪ ወረቀቱን ለማረሚያ ቤቱ ጸሀፊዎች በአግባቡ ሰጥቻለሁ ለምን እንዲቀርቡ እንዳላደረጉ  አልገባኝም፣ ወረቀቱ አልደረሰንም በማለት ሸምጥጠው ክደዋል፣ በማረሚያ ቤቱ እንዲህ አይነት መካካድ ያለ ነው ” በማለት ተናግራ ፣ ዛሬ የመጣሁት ተለዋጭ ጊዜ ቀጠሮ ለመውሰድ ነው ብላለች።

ፍርድቤቱም ተከሳሾች ባልቀረቡበት ችሎት ለመጋቢት 30 ቀን 2005 ዓም የጊዜ ቀጠሮ ሰጥቷል።

ችሎቱ ከተበተነ በሁዋላ የቃሊቲ ማረሚያ ቤት ፖሊሶች እነ አቶ ናትናኤል መኮንንን፣ አንዱአልም አያሌውን፣ አቶ ክንፈ ሚካኤል ደበበን ፣ አቶ ዮሐንስ ተረፈንና፣ ሻምበል የሽዋስ ይሁን አለምን ይዘው የመጡ ሲሆን፣ ቢሆንም ወዲያው መልሰው ወደ እስር ቤት ወስደዋቸዋል። ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋንና አቶ አንዱአለም አራጌን ግን  ማረሚያ ቤቱ ፍርድ ቤት ሳያቀርባቸው ቀርቷል።

ጠበቆች ለኢሳት እንደገለጡት እስረኞች ምንም አይነት የሽብርተኝነት ወንጀል ያልሰሩ መሆናቸው እየታወቀ መንግስት ስለከሰሳቸው ብቻ ወንጀለኞች ተብለው በግፍ ለእስር ተዳርገዋል።

Posted by Hellen Tesfaye

Leave a comment